Skip to content
Opens in a new window
Listen to this chapter • 5:32

[1] እንግዲህ እላለሁ፤ እግዚአብሔር ሕዝቡን ጣላቸውን? አይደለም፤ እኔ ደግሞ ከአብርሃም ዘር ከብንያም ወገን የሆንሁ እስራኤላዊ ነኝ።

[2] እግዚአብሔር አስቀድሞ ያወቃቸውን ሕዝቡን አልጣላቸውም፤ ኤልያስ እስራኤልን ወደ እግዚአብሔር እንዲህ ሲል በከሰሳቸው ጊዜ መጽሐፍ ያለውን አታውቁምን?

[3] “አቤቱ፥ ነቢያትህን ገደሉ፤ መሠዊያዎችህንም አፈረሱ፤ እኔም ብቻዬን ቀረሁ፤ ነፍሴንም ይሿታል።”

[4] የተገለጠለትስ ምን አለው? “ለጣዖት ያልሰገዱ ሰባት ሺህ ሰዎች ለእኔ አስቀርቻለሁ።”

[5] እንዲሁም ዛሬ በዚህ ዘመን በጸጋ የተመረጡና በእግዚአብሔር ያመኑ ቅሬታዎች አሉ።

[6] በጸጋ ከጸደቁ ግን በሥራቸው አይደለማ፤ በሥራም የሚጸድቁ ከሆነ ጸጋ ጸጋ አይባልም።

[7] እንግዲህ ምንድን ነው? እስራኤል የፈለገውን አላገኘም። የተመረጠው ግን አግኝቶአል፤ የቀሩትም ታወሩ።

[8] መጽሐፍ እንዳለ ፥ “እስከ ዛሬ ድረስ በዐይናቸው እንዳያዩ በጆሮአቸውም እንዳይሰሙ እግዚአብሔር ደንዛዛ አእምሮን ሰጣቸው።”

[9] ዳዊትም እንዲህ ብሎአል ፥ “ማዕዳቸው በፊታቸው ወጥመድና አሽክላ፥ መሰናከያና ፍዳም ትሁንባቸው።

[10] እንዳያዩ ዐይኖቻቸው ይጨልሙ፤ ዘወትርም ጀርባቸው ይጕuበጥ።”

[11] እንግዲህ እላለሁ፤ ሊወድቁ ተሰናከሉን? አይደለም፤ ነገር ግን እስራኤል ይቀኑ ዘንድ እነርሱ በመሰናከላቸው ለአሕዛብ ድኅነት ሆነ።

[12] የእነርሱ መሰናከል ለዓለም ባለጸግነት፥ በደላቸውም ለአሕዛብ ባለጸግነት ከሆነ ፍጹምነታቸውማ እንዴት በሆነ ነበር?

[13] ለእናንተ ለአሕዛብ እናገራለሁ፤ እኔ ለአሕዛብ ሐዋርያቸው እንደ መሆኔ መጠን መልእክቴን አከብራታለሁ።

[14] ይህም በዚህ ዘመዶቼን አስቀናቸው እንደ ሆነ፥ ከእነርሱ ወገን የሆኑትንም አድን እንደ ሆነ ነው።

[15] የእነርሱ መውጣት ለዓለም ዕርቅ ከሆነ ይልቁንም መመለሳቸው ምን ይሆን? ከሙታን በመነሣት የሚገኝ ሕይወት ነው።

[16] እርሾው ቅዱስ ከሆነ ቡሆውም እንዲሁ ቅዱስ ነው፤ ሥርዋ ቅዱስ ከሆነም ቅርንጫፎችዋ እንዲሁ ቅዱሳን ይሆናሉ።

[17] ከቅርንጫፎችዋ አንዳንዶቹ ቢሰበሩ የዱር ወይራ የሆንህ አንተን በእነርሱ ፋንታ ተከሉ፤ የእነርሱንም ሥርነት አገኘህ፤ እንደ እነርሱም ዘይት ሆንኽ።

[18] በቅርንጫፎች ላይ አትኵuራ፤ ብትኰራ ግን ሥሩ አንተን ይሸከምሃል እንጂ አንተ ሥሩን የምትሸከመው አይደለም።

[19] ቅርንጫፎችዋ ተሰበሩ፤ በእነርሱም ፋንታ “እኔ የዘይት ቅርንጫፍ ሆንሁ ” ትል ይሆናል።

[20] አላመኑምና ተሰበሩ፤ አንተ ግን ስለ አመንህ ቆመሃል፤ እንግዲህ ፈርተህ ኑር እንጂ ራስህን ከፍ ከፍ አታድርግ።

[21] እግዚአብሔር በተፈጥሮአቸው ቅርንጫፎች ለነበሩ ለእነዚያ ከአልራራላቸው ለአንተም አይራራልህም፤

[22] እንግዲህ የእግዚአብሔርን ርኅራኄውንና ጭካኔውን አስተውል፤ የወደቁትን ቀጣቸው፤ አንተን ግን ይቅር እንዳለህ ብትኖር ማረህ፤ ያለዚያ ግን አንተም ትቈረጣለህ።

[23] እነርሱም ባለማመናቸው ጸንተው ባይኖሩ ይተከላሉ። እግዚአብሔር ዳግመና ሊተክላቸው ይችላልና።

[24] አንተ የዱር ወይራ፥ አንተን ስንኳ ከበቀልህበት ቈርጦ ባልበቀልህበት በመልካሙ ዘይት ስፍራ ከተከለህ፥ ይልቁን ጥንቱን ዘይት የነበሩትን እነዚያን በበቀሉበት ስፍራ እንዴት አብልጦ ሊተክላቸው አይችልም?

[25] ወንድሞቻችን፥ እና ዐዋቂዎች ነን እንዳትሉ ይህን ምሥጢር ልታውቁ እወዳለሁ ፥ አሕዛብ ሁሉ እስኪገቡ ድረስ ከእስራኤል እኩሌቶችን የልብ ድንቐርና አግኝቶአቸዋልና።

[26] ከዚህ በኋላም መላው እስራኤል ይድናሉ፤ መጽሐፍ እንዲህ እንዳለ ፥ “አዳኝ ከጽዮን ይወጣል፤ ከያዕቆብም ኀጢአትን ያስወግዳል።

[27] ኀጢአታቸውንም ባራቅሁላቸው ጊዜ ከእነርሱ ጋር የምገባው ኪዳን ይህ ነው።”

[28] በወንጌል በኩል ስለ እናንተ ጠላቶቻችን ናቸው፤ በምርጫ በኩል ግን ስለ አባቶች ወዳጆች ናቸው።

[29] በእግዚአብሔር ጸጋና በመጥራቱ ጸጸት የለምና።

[30] ቀድሞ እናንተ እግዚአብሔርን እንደ አልታዘዛችሁት፥ ዛሬ ግን በእነርሱ አለመታዘዝ ይቅር እንዳላችሁ፥

[31] እንዲሁም እናንተ በተማራችሁት ምሕረት እነርሱ ምሕረትን እንዲያገኙ እነርሱ ዛሬ አልታዘዙትም።

[32] እግዚአብሔር ሁሉን ይቅር ይለው ዘንድ ሁሉን በኀጢአት ውስጥ ዘግቶታልና።

[33] የእግዚአብሔር ባለጠግነት፥ ጥበብና ዕውቀት እንዴት ጥልቅ ነው! ለመንገዱም ፍለጋ የለውም፤ ፍርዱንም የሚያውቀው የለም።

[34] “የእግዚአብሔርን ዐሳቡን ማን ያውቃል? ወይስ ማን ተማከረው?

[35] ብድሩን ይከፍል ዘንድ ለእርሱ አስቀድሞ ማን አበደረው?”

[36] ሁሉ ከእርሱ፥ በእርሱና ለእርሱ ነውና፤ ለእርሱም ለዘለዓለም ክብር ምስጋና ይሁን። አሜን።

ወደ ሮሜ ሰዎች። — Chapters