Skip to content
Opens in a new window

[1] ወደ ኢጣሊያም በመርከብ እንሄድ ዘንድ በተቈረጠ ጊዜ፥ ጳውሎስንና ሌሎችን እስረኞች ከአውግስጦስ ጭፍራ ለነበረ ዩልዮስ ለሚሉት ለመቶ አለቃ አሳልፈው ሰጡአቸው።

[2] በእስያም ዳርቻ ወዳሉ ስፍራዎች ይሄድ ዘንድ ባለው በአድራሚጢስ መርከብ ገብተን ተነሣን፤ የመቄዶንያም ሰው የሆነ የተሰሎንቄው አርስጥሮኮስ ከእኛ ጋር ነበረ።

[3] በነገውም ወደ ሲዶና ስንደርስ ዩልዮስ ለጳውሎስ ቸርነት አድርጎ እርዳታቸውን ይቀበል ዘንድ ወደ ወዳጆቹ እንዲሄድ ፈቀደለት።

[4] ከዚያም ተነሥተን ነፋሱ ፊት ለፊት ነበረና በቆጵሮስ ተተግነን ሄድን፤

[5] በኪልቅያና በጵንፍልያም አጠገብ ያለውን ባሕር ከተሻገርን በኋላ በሉቅያ ወዳለ ወደ ሙራ ደረስን።

[6] የመቶ አለቃውም በዚያ ወደ ኢጣሊያ የሚሄድ የእስክንድርያውን መርከብ አግኝቶ ወደ እርሱ አገባን።

[7] ብዙ ቀንም እያዘገምን ሄደን በጭንቅ ወደ ቀኒዶስ አንጻር ደረስን፤ ነፋስም ስለ ከለከለን በቀርጤስ ተተግነን በሰልሙና አንጻር ሄድን፤

[8] በጭንቅም ጥግ ጥጉን አልፈን ለላሲያ ከተማ ወደ ቀረበች መልካም ወደብ ወደሚሉአት ስፍራ መጣን።

[9] ብዙ ጊዜም ካለፈ በኋላ፥ የጦም ወራት አሁን አልፎ ስለ ነበረ በመርከብ ለመሄድ አሁን የሚያስፈራ ነበርና ጳውሎስ።

[10] እናንተ ሰዎች ሆይ፥ ይህ ጕዞ በጥፋትና በብዙ ጕዳት እንዲሆን አያለሁ፤ ጥፋቱም በገዛ ሕይወታችን ነው እንጂ በጭነቱና በመርከቡ ብቻ አይደለም ብሎ መከራቸው።

[11] የመቶ አለቃው ግን ጳውሎስ ከተናገረው ይልቅ የመርከብ መሪውንና የመርከቡን ባለቤት ያምን ነበር።

[12] ያም ወደብ ይከርሙበት ዘንድ የማይመች ስለ ሆነ፥ የሚበዙቱ ቢቻላቸው በሰሜንና በደቡብ ምዕራብ ትይዩ ወዳለው ፍንቄ ወደሚሉት ወደ ቀርጤስ ወደብ ደርሰው ይከርሙ ዘንድ ከዚያ እንዲነሡ መከሩ።

[13] ልከኛም የደቡብ ነፋስ በነፈሰ ጊዜ፥ እንዳሰቡት የሆነላቸው መስሎአቸው ተነሡ በቀርጤስም አጠገብ ጥግ ጥጉን አለፉ።

[14] ነገር ግን እጅግ ሳይዘገይ አውራቂስ የሚሉት ዓውሎ ነፋስ ከዚያ ወረደባቸው፤

[15] መርከቡም ተነጥቆ ነፋሱን ሲቃወም መሄድ ስላልቻለ ለቀነው ተነዳን።

[16] ቄዳ በሚሉአትም ደሴት በተተገንን ጊዜ ታንኳይቱን ለመግዛት በጭንቅ ቻልን፤

[17] ወደ ላይም ካወጡአት በኋላ መርከቡን በገመድ አስታጥቀው አጸኑ፤ ስርቲስም ወደሚሉት ወደ አሸዋ እንዳይወድቁ ፈርተው ሸራውን አውርደው እንዲሁ ተነዱ።

[18] ነፋሱም በርትቶ ሲያስጨንቀን በማንግሥቱ ከጭነቱ ወደ ባሕር ይጥሉ ነበር፥

[19] በሦስተኛውም ቀን የመርከቡን ዕቃ በእጃችን ወረወርን።

[20] ብዙ ቀንም ፀሐይን ከዋክብትንም ሳናይ ትልቅ ነፋስም ሲበረታብን ጊዜ፥ ወደ ፊት እንድናለን የማለት ተስፋ ሁሉ ተቈረጠ።

[21] ሳይበሉም ብዙ ቀን ከቆዩ በኋላ፥ ያን ጊዜ ጳውሎስ በመካከላቸው ቆሞ እንዲህ አለ። እናንተ ሰዎች ሆይ፥ ሰምታችሁኝ በሆነ ኖሮ ከቀርጤስ እንዳትነሡ ይህንም ጥፋትና ጕዳት እንዳታገኙ ይገባችሁ ነበር።

[22] አሁንም። አይዞአችሁ ብዬ እመክራችኋለሁ፤ ይህ መርከብ እንጂ ከእናንተ አንድ ነፍስ እንኳ አይጠፋምና።

[23] የእርሱ የምሆንና ደግሞ የማመልከው የእግዚአብሔር መልአክ በዚች ሌሊት በአጠገቤ ቆሞ ነበርና፥ እርሱም።

[24] ጳውሎስ ሆይ፥ አትፍራ፤ በቄሣር ፊት ልትቆም ይገባሃል፤ እነሆም፥ እግዚአብሔር ከአንተ ጋር የሚሄዱትን ሁሉ ሰጥቶሃል አለኝ።

[25] ስለዚህ እናንተ ሰዎች ሆይ፥ አይዞአችሁ፤ እንደ ተናገረኝ እንዲሁ እንዲሆን እግዚአብሔርን አምናለሁና።

[26] ነገር ግን ወደ አንዲት ደሴት እንድንወድቅ ያስፈልገናል።

[27] በአሥራ አራተኛውም ሌሊት በአድርያ ባሕር ወዲህና ወዲያ ስንነዳ፥ መርከበኞች በእኩለ ሌሊት ወደ አንድ ምድር የቀረቡ መሰላቸው።

[28] መለኪያ ገመድም ቢጥሉ ሀያ በሰው ቁመት አገኙ ጥቂትም ቆይተው ሁለተኛ ቢጥሉ አሥራ አምስት በሰው ቁመት አገኙ፤

[29] ድንጋያማም ወደ ሆነ ስፍራ እንዳይወድቁ ፈርተው፥ ከመርከቡ በስተኋላ አራት መልሕቅ አወረዱ፥ ቀንም እንዲሆን ተመኙ።

[30] መርከበኞቹም ከመርከቡ ይሸሹ ዘንድ ፈልገው ከመርከቡ በስተ ፊት መልሕቅ መጣል እንዳላቸው አመካኝተው ታንኳይቱን ወደ ባሕር ባወረዱ ጊዜ፥

[31] ጳውሎስ ለመቶ አለቃውና ለወታደሮቹ። እነዚህ በመርከቡ ካልቆዩ እናንተ ትድኑ ዘንድ አትችሉም አላቸው።

[32] ያን ጊዜ ወታደሮቹ የታንኳይቱን ገመድ ቈርጠው ትወድቅ ዘንድ ተዉአት።

[33] ቀንም ሲነጋ ጳውሎስ ምግብ ይበሉ ዘንድ ሁሉን ይለምን ነበር፥ እንዲህም አላቸው። እየጠበቃችሁ ምንም ሳትቀበሉ ጦማችሁን ከሰነበታችሁ ዛሬ አሥራ አራተኛ ቀናችሁ ነው።

[34] ሰለዚህ ምግብ ትበሉ ዘንድ እለምናችኋለሁ፤ ይህ ለደኅንነታችሁ ይሆናልና፤ ከእናንተ ከአንዱ የራስ ጠጕር እንኳ አትጠፋምና።

[35] ይህንም ብሎ እንጀራን ይዞ በሁሉ ፊት እግዚአብሔርን አመሰገነ ቈርሶም ይበላ ዘንድ ጀመረ።

[36] ሁለም ተጽናንተው ራሳቸው ደግሞ ምግብ ተቀበሉ።

[37] በመርከቡም ያለን ሁላችን ሁለት መቶ ሰባ ስድስት ነፍስ ነበርን።

[38] በልተውም በጠገቡ ጊዜ ስንዴውን ወደ ባሕር እየጣሉ መርከቡን አቃለሉት።

[39] በነጋም ጊዜ ምድሩን አላወቁትም፥ ነገር ግን የአሸዋ ዳር ያለውን የባሕር ስርጥ ተመለከቱ፥ ቢቻላቸውም መርከቡን ወደዚያ ይገፉ ዘንድ ቈረጡ።

[40] መልሕቆቹንም ፈትተው በባሕር ተዉአቸው፥ ያን ጊዜም የመቅዘፊያውን ማሠሪያ ፈቱት፤ ታናሹንም ሸራ ለነፋስ ከፍ አድርገው ወደ ዳር አቅንተው ይሄዱ ዘንድ ጀመሩ።

[41] ነገር ግን ሁለት ባሕር በተገናኙበት ስፍራ ወድቀው መርከቡን በዲብ ላይ ነዱ፤ በስተ ፊቱም ተተክሎ የማይነቃነቅ ሆነ፥ በስተ ኋላው ግን ከማዕበሉ ግፊያ የተነሣ ይሰበር ነበር።

[42] ወታደሮቹም ከእስረኞች አንድ ስንኳ ዋኝቶ እንዳያመልጥ ይገድሉአቸው ዘንድ ተማከሩ።

[43] የመቶ አለቃው ግን ጳውሎስን ያድነው ዘንድ አስቦ ምክራቸውን ከለከለ፤ ዋና የሚያውቁትም ከመርከብ ራሳቸውን እየወረወሩ አስቀድመው ወደ ምድር ይወጡ ዘንድ፥

[44] የቀሩትም እኵሌቶቹ በሳንቃዎች ላይ እኵሌቶቹም በመርከቡ ስባሪ ይወጡ ዘንድ አዘዘ። እንዲሁም ሁሉ በደኅና ወደ ምድር ደረሱ።

የሐዋርያት ሥራ። — Chapters