Skip to content
Opens in a new window

[1] በዓለ ኀምሳ የተባለውም ቀን በደረሰ ጊዜ፥ ሁሉም በአንድ ልብ ሆነው አብረው ሳሉ፥

[2] ድንገት እንደሚነጥቅ ዓውሎ ነፋስ ከሰማይ ድምፅ መጣ፥ ተቀምጠው የነበሩበትንም ቤት ሁሉ ሞላው።

[3] እንደ እሳትም የተከፋፈሉ ልሳኖች ታዩአቸው፤ በያንዳንዳቸውም ላይ ተቀመጡባቸው።

[4] በሁሉም መንፈስ ቅዱስ ሞላባቸው፥ መንፈስም ይናገሩ ዘንድ እንደ ሰጣቸው በሌላ ልሳኖች ይናገሩ ጀመር።

[5] ከሰማይም በታች ካሉ ሕዝብ ሁሉ በጸሎት የተጉ አይሁድ በኢየሩሳሌም ይኖሩ ነበር፤

[6] ይህም ድምፅ በሆነ ጊዜ ሕዝብ ሁሉ ተሰበሰቡ፥ እያንዳንዱም በገዛ ቋንቋው ሲናገሩ ይሰማ ስለ ነበር የሚሉትን አጡ።

[7] ተገርመውም ተደንቀውም እንዲህ አሉ። እነሆ፥ እነዚህ የሚናገሩት ሁሉ የገሊላ ሰዎች አይደሉምን?

[8] እኛም እያንዳንዳችን የተወለድንበትን የገዛ ቋንቋችንን እንዴት እንሰማለን?

[9] የጳርቴና የሜድ የኢላሜጤም ሰዎች፥ በሁለት ወንዝም መካከል በይሁዳም በቀጰዶቅያም በጳንጦስም በእስያም፥

[10] በፍርግያም በጵንፍልያም በግብፅም በቀሬናም በኩል ባሉት በሊቢያ ወረዳዎች የምንኖር፥ በሮሜም የምንቀመጥ፥ አይሁድም ወደ ይሁዲነትም የገባን፥

[11] የቀርጤስና የዓረብ ሰዎች፥ የእግዚአብሔርን ታላቅ ሥራ በልሳኖቻችን ሲናገሩ እንሰማቸዋለን።

[12] ሁሉም ተገረሙና አመንትተው እርስ በርሳቸው። እንጃ ይህ ምን ይሆን? አሉ።

[13] ሌሎች ግን እያፌዙባቸው። ጉሽ የወይን ጠጅ ጠግበዋል አሉ።

[14] ነገር ግን ጴጥሮስ ከአሥራ አንዱ ጋር ቆመ፥ ድምፁንም ከፍ አድርጎ እንዲህ ሲል ተናገራቸው። አይሁድ በኢየሩሳሌምም የምትኖሩ ሁላችሁ፥ ይህ በእናንተ ዘንድ የታወቀ ይሁን፥ ቃሎቼንም አድምጡ።

[15] ለእናንተ እንደ መሰላችሁ እነዚህ የሰከሩ አይደሉም፥ ከቀኑ ሦስተኛ ሰዓት ነውና፤

[16] ነገር ግን ይህ በነቢዩ በኢዩኤል የተባለው ነው።

[17] እግዚአብሔር ይላል። በመጨረሻው ቀን እንዲህ ይሆናል፤ ሥጋ በለበሰ ሁሉ ላይ ከመንፈሴ አፈሳለሁ፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁም ትንቢት ይናገራሉ፥ ጎበዞቻችሁም ራእይ ያያሉ፥ ሽማግሌዎቻችሁም ሕልም ያልማሉ፤

[18] ደግሞም በዚያች ወራት በወንዶችና በሴቶች ባሪያዎቼ ላይ ከመንፈሴ አፈሳለሁ ትንቢትም ይናገራሉ።

[19] ድንቆችን በላይ በሰማይ፥ ምልክቶችንም በታች በምድር እሰጣለሁ፤ ደምም እሳትም የጢስ ጭጋግም ይሆናል፤

[20] ታላቅ የሆነ የተሰማም የጌታ ቀን ሳይመጣ ፀሐይ ወደ ጨለማ ጨረቃም ወደ ደም ይለወጣሉ።

[21] የጌታን ስም የሚጠራም ሁሉ ይድናል።

[22] የእስራኤል ሰዎች ሆይ፥ ይህን ቃል ስሙ፤ ራሳችሁ እንደምታውቁ፥ የናዝሬቱ ኢየሱስ እግዚአብሔር በመካከላችሁ በእርሱ በኩል ባደረገው ተአምራትና በድንቆች በምልክቶችም ከእግዚአብሔር ዘንድ ለእናንተ የተገለጠ ሰው ነበረ፤

[23] እርሱንም በእግዚአብሔር በተወሰነው አሳቡና በቀደመው እውቀቱ ተሰጥቶ በዓመፀኞች እጅ ሰቅላችሁ ገደላችሁት።

[24] እግዚአብሔር ግን የሞትን ጣር አጥፍቶ አስነሣው፥ ሞት ይይዘው ዘንድ አልቻለምና።

[25] ዳዊት ስለ እርሱ እንዲህ ይላልና። ጌታን ሁልጊዜ በፊቴ አየሁት፥ እንዳልታወክ በቀኜ ነውና።

[26] ስለዚህ ልቤን ደስ አለው፥ ልሳኔም ሐሤት አደረገ፥ ደግሞም ሥጋዬ በተስፋ ያድራል፤

[27] ነፍሴን በሲኦል አትተዋትምና፥ ቅዱስህንም መበስበስን ያይ ዘንድ አትሰጠውም።

[28] የሕይወትን መንገድ አስታወቅኸኝ፤ ከፊትህ ጋር ደስታን ትሞላብኛለህ።

[29] ወንድሞች ሆይ፥ ስለ አባቶች አለቃ ስለ ዳዊት እንደ ሞተም እንደ ተቀበረም ለእናንተ በግልጥ እናገር ዘንድ ፍቀዱልኝ፤ መቃብሩም እስከ ዛሬ በእኛ ዘንድ ነው።

[30] ነቢይ ስለ ሆነ፥ ከወገቡም ፍሬ በዙፋኑ ያስቀምጥ ዘንድ እግዚአብሔር መሐላ እንደ ማለለት ስለ አወቀ፥

[31] ስለ ክርስቶስ ትንሣኤ አስቀድሞ አይቶ፥ ነፍሱ በሲኦል እንዳልቀረች ሥጋውም መበስበስን እንዳላየ ተናገረ።

[32] ይህን ኢየሱስን እግዚአብሔር አስነሣው ለዚህም ነገር እኛ ሁላችን ምስክሮች ነን፤

[33] ስለዚህ በእግዚአብሔር ቀኝ ከፍ ከፍ ብሎና የመንፈስ ቅዱስን የተስፋ ቃል ከአብ ተቀብሎ ይህን እናንተ አሁን የምታዩትንና የምትሰሙትን አፈሰሰው።

[34] -

[35] ዳዊት ወደ ሰማያት አልወጣምና፥ ነገር ግን እርሱ። ጌታ ጌታዬን። ጠላቶችህን የእግርህ መረገጫ እስካደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ አለው

[36] አለ። እንግዲህ ይህን እናንተ የሰቀላችሁትን ኢየሱስን እግዚአብሔር ጌታም ክርስቶስም እንዳደረገው የእስራኤል ወገን ሁሉ በእርግጥ ይወቅ።

[37] ይህንም በሰሙ ጊዜ ልባቸው ተነካ፥ ጴጥሮስንና ሌሎችንም ሐዋርያት። ወንድሞች ሆይ፥ ምን እናድርግ? አሉአቸው።

[38] ጴጥሮስም። ንስሐ ግቡ፥ ኃጢአታችሁም ይሰረይ ዘንድ እያንዳንዳችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ፤ የመንፈስ ቅዱስንም ስጦታ ትቀበላላችሁ።

[39] የተስፋው ቃል ለእናንተና ለልጆቻችሁ ጌታ አምላካችንም ወደ እርሱ ለሚጠራቸው በሩቅ ላሉ ሁሉ ነውና አላቸው።

[40] በብዙ ሌላ ቃልም መሰከረና። ከዚህ ጠማማ ትውልድ ዳኑ ብሎ መከራቸው።

[41] ቃሉንም የተቀበሉ ተጠመቁ፥ በዚያም ቀን ሦስት ሺህ የሚያህል ነፍስ ተጨመሩ፤

[42] በሐዋርያትም ትምህርትና በኅብረት እንጀራውንም በመቍረስ በየጸሎቱም ይተጉ ነበር።

[43] ነገር ግን በሰው ሁሉ ፍርሀት ሆነ፤ በሐዋርያትም እጅ ብዙ ድንቅና ምልክት ተደረገ።

[44] ያመኑትም ሁሉ አብረው ነበሩ፤

[45] ያላቸውንም ሁሉ አንድነት አደረጉ። መሬታቸውንና ጥሪታቸውንም እየሸጡ፥ ማንኛውም እንደሚፈልግ ለሁሉ ያካፍሉት ነበር።

[46] በየቀኑም በአንድ ልብ ሆነው በመቅደስ እየተጉ በቤታቸውም እንጀራ እየቈረሱ፥ በደስታና በጥሩ ልብ ምግባቸውን ይመገቡ ነበር፤

[47] እግዚአብሔርንም እያመሰገኑ በሕዝብ ሁሉ ፊት ሞገስ ነበራቸው። ጌታም የሚድኑትን ዕለት ዕለት በእነርሱ ላይ ይጨምር ነበር።

የሐዋርያት ሥራ። — Chapters