[1] ፊስጦስም ወደ አውራጃው ገብቶ ከሦስት ቀን በኋላ ከቂሣርያ ወደ ኢየሩሳሌም ወጣ።
[2] የካህናቱ አለቆችና የአይሁድም ታላላቆች በጳውሎስ ላይ አመለከቱ፥
[3] ጳውሎስንም ሲቃወም እንዲያደላላቸው እየለመኑ፥ በመንገድ ሸምቀው ይገድሉት ዘንድ አስበው ወደ ኢየሩሳሌም እንዲያስመጣው ማለዱት።
[4] ፊስጦስ ግን ጳውሎስ በቂሳርያ እንዲጠበቅ እርሱም ራሱ ወደዚያ ፈጥኖ ይሄድ ዘንድ እንዳለው መለሰላቸው፤
[5] እንግዲህ በዚህ ሰው ክፋት ቢሆን ከእናንተ ዘንድ ያሉት ባለ ስልጣኖች ከእኔ ጋር ወርደው ይክሰሱት አላቸው።
[6] በእነርሱም ዘንድ ከስምንት ወይም ከአስር የማይበልጥ ቀን ተቀምጦ ወደ ቂሳርያ ወረደ፤ በነገውም በፍርድ ወንበር ተቀምጦ ጳውሎስን ያመጡት ዘንድ አዘዘ።
[7] በቀረበም ጊዜ ከኢየሩሳሌም የወረዱት አይሁድ ከበውት ቆሙ፥ ይረቱበትም ዘንድ የማይችሉትን ብዙና ከባድ ክስ አነሱበት፤
[8] ጳውሎስም ሲምዋገት። የአይሁድን ህግ ቢሆን መቅደስንም ቢሆን ቄሳርንም ቢሆን አንዳች ስንኳ አልበደልሁም አለ።
[9] ፊስጦስ ግን አይሁድን ደስ ያሰኝ ዘንድ ወዶ ጳውሎስን። ወደ ኢየሩሳሌም ወጥተህ ስለዚህ ነገር ከዚያው በፊቴ ትፋረድ ዘንድ ትወዳለህን? ብሎ መለሰለት።
[10] ጳውሎስ ግን። እፋረድበት ዘንድ በሚገባኝ በቄሳር ፍርድ ወንበር ፊት ቆሜአለሁ። አንተው ደግሞ ፈጽመህ እንደምታውቅ አይሁድን ምንም አልበደልሁም።
[11] እንግዲህ በድዬ ወይም ሞት የሚገባውን ነገር አድርጌ እንደ ሆነ ከሞት ልዳን አልልም፤ እነዚህ የሚከሱኝ ክስ ከንቱ እንደሆነ ግን ለእነርሱ አሳልፎ ይሰጠኝ ዘንድ ማንም አይችልም፤ ወደ ቄሳር ይግባኝ ብዬአለሁ አለ።
[12] በዚያን ጊዜ ፊስጦስ ከአማካሪዎቹ ጋር ተማክሮ። ወደ ቄሳር ይግባኝ ብለሃል፤ ወደ ቄሳር ትሄዳለህ ብሎ መለሰለት።
[13] ከጥቂት ቀንም በኋላ ንጉሡ አግሪጳ በርኒቄም ለፊስጦስ ሰላምታ እንዲያቀርቡ ወደ ቂሳርያ ወረዱ።
[14] በዚያውም ብዙ ቀን ስለተቀመጡ ፊስጦስ የጳውሎስን ነገር ለንጉሡ እንዲህ ብሎ ገለጠ። ፊልክስ አስሮ የተወው አንድ ሰው በዚህ አለ፤
[15] በኢየሩሳሌምም ሳለሁ የካህናት አለቆችና የአይሁድ ሽማግሌዎች እፈርድበት ዘንድ እየለመኑ ስለ እርሱ አመለከቱኝ።
[16] እኔም። ተከሳሹ በከሳሾቹ ፊት ለፊት ሳይቆም ለተከሰሰበትም መልስ ይሰጥ ዘንድ ፈንታ ሳያገኝ፥ ማንንም ቢሆን አሳልፎ መስጠት የሮማውያን ሥርዓት አይደለም ብዬ መለስሁላቸው።
[17] ስለዚህም በዚህ በተሰበሰቡ ጊዜ፥ ሳልዘገይ በማግሥቱ በፍርድ ወንበር ተቀምጬ ያንን ሰው ያመጡት ዘንድ አዘዝሁ።
[18] ከሳሾቹም በቆሙ ጊዜ እኔ ያሰብሁትን ክፉ ነገር ክስ ምንም አላመጡበትም፤
[19] ነገር ግን ስለ ገዛ ሃይማኖታቸውና ጳውሎስ። ሕያው ነው ስለሚለው ስለ ሞተው ኢየሱስ ስለ ተባለው ከእርሱ ጋር ይከራከሩ ነበር።
[20] እኔም ይህን ነገር እንዴት እንድመረምር አመንትቼ። ወደ ኢየሩሳሌም ሄደህ በዚህ ነገር ከዚያ ልትፋረድ ትወዳለህን? አልሁት።
[21] ጳውሎስ ግን አውግስጦስ ቄሣር እስኪቈርጥ ድረስ እንዲጠበቅ ይግባኝ ባለ ጊዜ፥ ወደ ቄሣር እስክሰደው ድረስ ይጠበቅ ዘንድ አዘዝሁ።
[22] አግሪጳም ፊስጦስን። ያንንስ ሰው እኔ ዳግም እኮ እሰማው ዘንድ እወድ ነበር አለው። እርሱም። ነገ ትሰማዋለህ አለው።
[23] በነገውም አግሪጳና በርኒቄ በብዙ ግርማ መጥተው ከሻለቆችና ከከተማው ታላላቆች ጋር ወደ ፍርድ ቤት ገቡ፤ ፊስጦስም ባዘዘ ጊዜ ጳውሎስን አመጡት።
[24] ፊስጦስም አለ። አግሪጳ ንጉሥ ሆይ እናንተም ከእኛ ጋር ያላችሁ ሰዎች ሁሉ፥ ከእንግዲህ ወዲህ በሕይወት ይኖር ዘንድ እንዳይገባው እየጮኹ የአይሁድ ሕዝብ ሁሉ በኢየሩሳሌም በዚህም ስለ እርሱ የለመኑኝን ይህን ሰው ታዩታላችሁ።
[25] እኔ ግን ሞት የሚገባውን ነገር እንዳላደረገ አስተዋልሁ፥ እርሱም ወደ አውግስጦስ ይግባኝ ስላለ እሰደው ዘንድ ቈረጥሁ።
[26] ስለ እርሱም ወደ ጌታዬ የምጽፈው እርግጥ ነገር የለኝም፤ ስለዚህ ከተመረመረ በኋላ የምጽፈውን ነገር አገኝ ዘንድ በፊታችሁ ይልቁንም በፊትህ፥ ንጉሥ አግሪጳ ሆይ፥ አመጣሁት፤
[27] እስረኛ ሲላክ የተከሰሰበትን ምክንያት ደግሞ አለማመልከት ሞኝነት መስሎኛልና።