[1] በአንጾኪያም ባለችው ቤተ ክርስቲያን ነቢያትና መምህራን ነበሩ፤ እነርሱም በርናባስ፥ ኔጌር የተባለው ስምዖንም፥ የቀሬናው ሉክዮስም፥ የአራተኛው ክፍል ገዥ የሄሮድስም ባለምዋል ምናሔ፥ ሳውልም ነበሩ።
[2] እነዚህም ጌታን ሲያመልኩና ሲጦሙ መንፈስ ቅዱስ። በርናባስንና ሳውልን ለጠራኋቸው ሥራ ለዩልኝ አለ።
[3] በዚያን ጊዜም ከጦሙ ከጸለዩም እጃቸውንም ከጫኑ በኋላ አሰናበቱአቸው።
[4] እነርሱም በመንፈስ ቅዱስ ተልከው ወደ ሴሌውቅያ ወረዱ፤ ከዚያም በመርከብ ወደ ቆጵሮስ ሄዱ።
[5] በስልማናም በነበሩ ጊዜ በአይሁድ ምኵራቦች የእግዚአብሔርን ቃል ሰበኩ፤ አገልጋይም ዮሐንስ ነበራቸው።
[6] ደሴቲቱንም ሁሉ እስከ ጳፉ በዞሩ ጊዜ፥ በርያሱስ የሚሉትን ጠንቋይና ሐሰተኛ ነቢይ የሆነውን አንድ አይሁዳዊ ሰው አገኙ፤
[7] እርሱም አስተዋይ ሰው ከሆነው ሰርግዮስ ጳውሎስ ከሚባለው አገረ ገዥ ጋር ነበረ። ይህም በርናባስንና ሳውልን ወደ እርሱ ጠርቶ የእግዚአብሔርን ቃል ሊሰማ ፈለገ።
[8] ጠንቋዩ ግን ኤልማስ፥ ስሙ እንዲሁ ይተረጐማልና፥ አገረ ገዡን ከማመን ሊያጣምም ፈልጎ ተቃወማቸው።
[9] ጳውሎስ የተባለው ሳውል ግን መንፈስ ቅዱስን ተሞልቶ ትኵር ብሎ ሲመለከተው።
[10] አንተ ተንኰል ሁሉ ክፋትም ሁሉ የሞላብህ፥ የዲያብሎስ ልጅ፥ የጽድቅም ሁሉ ጠላት፥ የቀናውን የጌታን መንገድ ከማጣመም አታርፍምን?
[11] አሁንም፥ እነሆ፥ የጌታ እጅ በአንተ ላይ ናት፥ ዕውርም ትሆናለህ እስከ ጊዜውም ፀሐይን አታይም አለው። ያን ጊዜም ጭጋግና ጨለማ ወደቀበት፥ በእጁም የሚመራውን እየዞረ ፈለገ።
[12] በዚያን ጊዜ አገረ ገዡ የተደረገውን ባየ ጊዜ ከጌታ ትምህርት የተነሣ ተገርሞ አመነ።
[13] ጳውሎስም ከጓደኞቹ ጋር ከጳፉ ተነሥቶ የጵንፍልያ ወደምትሆን ወደ ጴርጌን መጣ፤ ዮሐንስም ከእነርሱ ተለይቶ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሰ።
[14] እነርሱ ግን ከጴርጌን አልፈው የጲስድያ ወደምትሆን ወደ አንጾኪያ ደረሱ፤ በሰንበትም ቀን ወደ ምኵራብ ገብተው ተቀመጡ።
[15] ሕግና ነቢያትም ከተነበቡ በኋላ የምኵራቡ አለቆች። ወንድሞች ሆይ፥ ሕዝብን የሚመክር ቃል እንዳላችሁ ተናገሩ ብለው ላኩባቸው።
[16] ጳውሎስም ተነሣና በእጁ ጠቅሶ እንዲህ አለ። የእስራኤል ሰዎችና እግዚአብሔርን የምትፈሩት ሆይ፥ ስሙ።
[17] የዚህ የእስራኤል ሕዝብ አምላክ አባቶቻችንን መርጦ በግብፅ አገር በእንግድነት ሳሉ ሕዝቡን ከፍ ከፍ አደረጋቸው፥ ከፍ ባለችውም ክንዱ ከዚያ አወጣቸው።
[18] በበረሀም አርባ ዓመት ያህል መገባቸው።
[19] በከነዓንም አገር ሰባት አሕዛብን አጥፍቶ ምድራቸውን አወረሳቸው።
[20] ከዚህም በኋላ እስከ ነቢዩ እስከ ሳሙኤል ድረስ አራት መቶ አምሳ ዓመት ያህል መሳፍንትን ሰጣቸው።
[21] ከዚያም ወዲያ ንጉሥን ያነግሥላቸው ዘንድ ለመኑ፥ እግዚአብሔርም ከብንያም ወገን የሚሆን ሰው የቂስን ልጅ ሳኦልን አርባ ዓመት ሰጣቸው፤
[22] እርሱንም ከሻረው በኋላ ዳዊትን በእነርሱ ላይ እንዲነግሥ አስነሣው፥ ሲመሰክርለትም። እንደ ልቤ የሆነ ሰው ፈቃዴንም ሁሉ የሚያደርግ የእሴይን ልጅ ዳዊትን አገኘሁ አለ።
[23] ከዚህም ሰው ዘር እግዚአብሔር እንደ ተስፋው ቃል ለእስራኤል መድኃኒትን እርሱም ኢየሱስን አመጣ።
[24] ከመምጣቱ በፊት ዮሐንስ አስቀድሞ ለእስራኤል ሕዝብ ሁሉ የንስሐን ጥምቀት ሰብኮ ነበር።
[25] ዮሐንስም ሩጫውን ሲፈጽም ሳለ። እኔ ማን እንደ ሆንሁ ታስባላችሁ? እኔስ እርሱን አይደለሁም፤ ነገር ግን እነሆ፥ የእግሩን ጫማ እፈታ ዘንድ ከማይገባኝ ከእኔ በኋላ ይመጣል ይል ነበር።
[26] እናንተ ወንድሞቻችን፥ የአብርሃም ዘር ልጆች ከእናንተ መካከልም እግዚአብሔርን የምትፈሩ ሆይ፥ ለእናንተ የዚህ የመዳን ቃል ተላከ።
[27] በኢየሩሳሌም የሚኖሩ ሰዎችና አለቆቻቸው እርሱንና በየሰንበቱ የሚነበቡትን የነቢያትን ድምፆች ስላላወቁ በፍርዳቸው ፈጽመዋልና፤
[28] ለሞትም የሚያደርስ ምክንያት አንድ ስንኳ ባያገኙበት፥ ይገድለው ዘንድ ጲላጦስን ለመኑት፤
[29] ስለ እርሱም የተጻፈውን ሁሉ በፈጸሙ ጊዜ ከእንጨት አውርደው በመቃብር አኖሩት።
[30] እግዚአብሔር ግን ከሙታን አስነሣው፤
[31] በሕዝብም ዘንድ ምስክሮቹ ለሆኑት ከእርሱ ጋር ከገሊላ ወደ ኢየሩሳሌም ለወጡት ብዙ ቀን ታያቸው።
[32] እኛም ለአባቶች የተሰጠውን ተስፋ የምስራቹን ለእናንተ እንሰብካለን፤
[33] ይህን ተስፋ እግዚአብሔር በሁለተኛው መዝሙር ደግሞ። አንተ ልጄ ነህ እኔ ዛሬ ወለድሁህ ተብሎ እንደ ተጻፈ፥ ኢየሱስን አስነሥቶ ለእኛ ለልጆቻቸው ፈጽሞአልና።
[34] እንደገናም ወደ መበስበስ እንዳይመለስ ከሙታን እንደ አስነሣው፥ እንዲህ። የታመነውን የዳዊትን ቅዱስ ተስፋ እሰጣችኋለሁ ብሎአል።
[35] ደግሞ በሌላ ስፍራ። ቅዱስህን መበስበስን ያይ ዘንድ አትሰጠውም ይላልና።
[36] ዳዊትም በራሱ ዘመን የእግዚአብሔርን አሳብ ካገለገለ በኋላ አንቀላፋ፥ ከአባቶቹም ጋር ተጨምሮ መበስበስን አየ፤
[37] ይህ እግዚአብሔር ያስነሣው ግን መበስበስን አላየም።
[38] -
[39] እንግዲህ ወንድሞች ሆይ፥ በእርሱ በኩል የኃጢአት ስርየት እንዲነገርላችሁ፥ በሙሴም ሕግ ትጸድቁበት ዘንድ ከማይቻላችሁ ሁሉ ያመነ ሁሉ በእርሱ እንዲጸድቅ በእናንተ ዘንድ የታወቀ ይሁን።
[40] -
[41] እንግዲህ። እናንተ የምትንቁ፥ እዩ ተደነቁም ጥፉም አንድ ስንኳ ቢተርክላችሁ የማታምኑትን ሥራ በዘመናችሁ እኔ እሠራለሁና ተብሎ በነቢያት የተነገረው እንዳይደርስባችሁ ተጠንቀቁ።
[42] በወጡም ጊዜ ይህን ነገር በሚመጣው ሰንበት ይነግሩአቸው ዘንድ ለመኑአቸው።
[43] ጉባኤውም ከተፈታ በኋላ ከአይሁድና ወደ ይሁዲነት ገብተው ከሚያመልኩ ብዙዎች ጳውሎስንና በርናባስን ተከተሉአቸው፥ እነርሱም ሲነግሩአቸው በእግዚአብሔር ጸጋ ጸንተው እንዲኖሩ አስረዱአቸው።
[44] በሁለተኛውም ሰንበት ከጥቂቶቹ በቀር የከተማው ሰው ሁሉ የእግዚአብሔርን ቃል ይሰሙ ዘንድ ተሰበሰቡ።
[45] አይሁድም ብዙ ሕዝብ ባዩ ጊዜ ቅንዓት ሞላባቸው፥ እየተሳደቡም ጳውሎስ የተናገረውን ቃል ተቃወሙ።
[46] ጳውሎስና በርናባስም ገልጠው። የእግዚአብሔር ቃል አስቀድሞ ለእናንተ ይነገር ዘንድ ያስፈልጋል፤ ከገፋችሁትና የዘላለም ሕይወት እንዳይገባችሁ በራሳችሁ ከፈረዳችሁ ግን፥ እነሆ፥ ወደ አሕዛብ ዘወር እንላለን።
[47] እንዲሁ ጌታ። እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ለማዳን ትሆን ዘንድ ለአሕዛብ ብርሃን አድርጌሃለሁ ብሎ አዞናልና አሉ።
[48] አሕዛብም ሰምተው ደስ አላቸው የእግዚአብሔርንም ቃል አከበሩ፥ ለዘላለም ሕይወትም የተዘጋጁ ሁሉ አመኑ፤
[49] የጌታም ቃል በአገሩ ሁሉ ተስፋፋ።
[50] አይሁድ ግን የሚያመልኩትን የከበሩትንም ሴቶችና የከተማውን መኳንንት አወኩ፥ በጳውሎስና በበርናባስም ላይ ስደትን አስነሥተው ከአገራቸው አወጡአቸው።
[51] እነርሱ ግን የእግራቸውን ትቢያ አራግፈውባቸው ወደ ኢቆንዮን መጡ።
[52] በደቀ መዛሙርትም ደስታና መንፈስ ቅዱስ ሞላባቸው።