Skip to content
Opens in a new window
Listen to this chapter • 3:58

[1] አሁንም የተወደዳችሁና የምናፍቃችሁ ወንድሞቻችን ሆይ፥ ደስታችንና አክሊላችን ናችሁ፤ ወዳጆቻችን ሆይ፥ እንዲህ ቁሙ፤ በጌታችንም ጽኑ።

[2] ኤዎድያና ስንጣክን ሆይ፥ በአንድ ልብ ጌታችንን ለማገልገል ታስቡ ዘንድ እማልዳችኋለሁ።

[3] ወንድሜና አጋዤ ስትሪካ ሆይ፥ እንድትረዳቸው አንተንም እለምንሃለሁ፤ ወንጌልን በማስተማር ከቀሌምንጦስና ሥራቸው ከተባበረ፥ ስማቸውም በሕይወት መጽሐፍ ከተጻፈላቸው ከወንድሞቻችንም ሁሉ ጋር ከእኔም ጋር ደክመዋልና።

[4] ዘወትር በጌታችን ደስ ይበላችሁ፤ ደግሜ እላችኋለሁ ፥ ደስ ይበላችሁ።

[5] ፍጹምነታችሁም በሰው ሁሉ ዘንድ ይታወቅ። እግዚአብሔር ቅርብ ነው፤

[6] በምንም አትጨነቁ፤ ነገር ግን በሁሉ ነገር ጸልዩ ማልዱም፤ እያመሰገናችሁም ልመናችሁን ለእግዚአብሔር ግለጡ።

[7] ሁሉ የሚገኝባት፥ ከልቡናና ከአሳብ ሁሉ በላይ የምትሆን የእግዚአብሔር ሰላም በኢየሱስ ክርስቶስ ልባችሁንና አሳባችሁን ታጽናው።

[8] አሁንም ወንድሞቻችን ሆይ፥ እውነትን ሁሉ፥ ቅንነትንም ሁሉ፥ ጽድቅንም ሁሉ፥ ንጽሕናንም ሁሉ፥ ፍቅርንና ስምምነትንም ሁሉ፥ በጎነትም ቢሆን፥ ምስጋናም ቢሆን፥ እነዚህን ሁሉ አስቡ።

[9] ከእኔ የተማራችሁትንና የተቀበላችሁትን፥ የሰማችሁትንና ያያችሁትንም እነዚህን አድርጉ፤ የሰላም አምላክም ከሁላችሁ ጋር ይሆናል።

[10] በጌታችን እጅግ ደስ አለኝ፤ ቢሳናችሁ እንኳ አሁንም እንደምታስቡልኝ፥ ከዱሮ ጀምሮ ለእኔ ችግር ታስቡ፥ ትተጉም ነበርና።

[11] ይህንም የምል ስለ አጣሁ አይደለም፤ ያለኝ እንደሚበቃኝ አውቃለሁና።

[12] እኔ ችግሩንም፥ ምቾቱንም እችላለሁ፤ ራቡንም፥ ጥጋቡንም፥ ማዘኑንም፥ ደስታውንም፥ ሁሉን በሁሉ ለምጀዋለሁ፤

[13] በሚያስችለኝ በክርስቶስ ሁሉን እችላለሁ።

[14] ነገር ግን በመከራዬ ጊዜ ተባባሪዎች መሆናችሁ መልካም አደረጋችሁ።

[15] እናንተ የፊልጵስዩስ ሰዎች፤ በመጀመሪያው ትምህርት ከመቄዶንያ ወደ እናንተ በመጣሁ ጊዜ፥ ከእናንተ ብቻ በቀር ሌላ ቤተ ክርስቲያን በመስጠትም ቢሆን፥ በመቀበል ከእኔ ጋር እንዳልተባበሩ እናንተ ታውቃላችሁ።

[16] በተሰሎንቄም ሳለሁ ደግሞ፥ አንድ ጊዜና ሁለት ጊዜ ለችግሬ ላካችሁልኝ።

[17] ይህንም የማነሣሣው ስጦታችሁን ፈልጌ አይደለም፤ በእናንተ ላይ የጽድቅ ፍሬ ይበዛ ዘንድ ፈልጌ ነው እንጂ።

[18] ነገር ግን ሁሉ አለኝ፤ ይበዛልኝማል፤ የመዓዛ ሽታና የተወደደ መሥዋዕት የሚሆነውን፥ ለእግዚአብሔርም ደስ የሚያሰኘውን ስጦታችሁን ከአፍሮዲጡ ተቀብዬ አሟልቻለሁ።

[19] ፈጣሪዬ እንደ ባለጸግነቱ መጠን፥ በክብር በኢየሱስ ክርስቶስ የምትሹትን ሁሉ ይፈጽምላችኋል።

[20] ለአባታችን ለእግዚአብሔር ለዘለዓለሙ ምስጋና ይሁን አሜን።

[21] በኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱሳንን ሁሉ ሰላም በሉ፤ በእኔ ዘንድ ያሉ ወንድሞቻችንም ሰላምታ ያቀርቡላችኋል።

[22] ቅዱሳንም ሁሉ፥ ይልቁንም ከቄሣር ቤተ ሰብእ የሆኑ ሰላምታ ያቀርቡላችኋል።

[23] የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከእናንተ ጋር ይሁን፤ አሜን። በሮሜ ተጽፋ በጢሞቴዎስና በአፍሮዲጡ እጅ ወደ ፊልጵስዩስ ሰዎች የተላከች መልእክት ተፈጸመች። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን አሜን።

ወደ ፊልጵስዩስ ሰዎች። — Chapters