Skip to content
Opens in a new window
Listen to this chapter • 4:00

[1] አሁንም በክርስቶስ ደስታ፥ ወይም በፍቅር የልብ መጽናናት፥ ወይም የመንፈስ አንድነት፥ ወይም ማዘንና መራራትም በእናንተ ዘንድ ካለ ፥

[2] እርሱን ብቻ ታስቡ ዘንድ፥ አንድ ልብና አንድ ምክርም ሆናችሁ፥ በፍቅር ትኖሩ ዘንድ ደስታዬን ፈጽሙልኝ።

[3] በክርክርና ከንቱ ውዳሴን በመውደድ አትሥሩ፤ ትሕትናን በያዘ ልቡና ከራሳችሁ ይልቅ ባልንጀራችሁን አክብሩ እንጂ አትታበዩ።

[4] ለባልንጀራችሁም እንጂ ለየራሳችሁ ብቻ አታስቡ።

[5] ፍጹማን የሆናችሁ ሁላችሁ ኢየሱስ ክርስቶስ ለእኛ እንደ አደረገልን ይህን አስቡ።

[6] ይኸውም የእግዚአብሔር መልኩ ነው፤ ቀምቶ እግዚአብሔር የሆነ አይደለም።

[7] ነገር ግን የባርያን መልክ ይዞ፥ በሰውም ምሳሌ ሆኖ ራሱን ዝቅ አደረገ።

[8] እንደ ሰውም ሆኖ ራሱን አዋረደ፤ ለሞት እስከ መድረስም ታዘዘ፤ ሞቱም በመስቀል የሆነው ነው።

[9] ስለዚህም እግዚአብሔር እጅግ ከፍ ከፍ አደረገው፤ ከስም ሁሉ የሚበልጥ ስምንም ሰጠው።

[10] ይህም በሰማይና በምድር በቀላያትና ከምድር በታች ያለ ጕuልበት ሁሉ ለኢየሱስ ክርስቶስ ስም ይሰግድ ዘንድ ነው።

[11] አንደበትም ሁሉ ኢየሱስ ክርስቶስ በእግዚአብሔር አብ ክብር ጌታ እንደ ሆነ ያምን ዘንድ ነው።

[12] አሁንም ወንድሞቼ ሆይ፥ ዘወትር እንደምትሰሙኝ ሳለሁ ብቻ ሳይሆን፥ ሳልኖርም በፍርሀትና በመንቀጥቀጥ ሆናችሁ ለድኅነታችሁ ሥሩ።

[13] ለሚወደው ሥራ የሚረዳችሁ እርሱ እግዚአብሔር ይቅርታውን ይፈጽምላችሁ።

[14] የምትሠሩትን ሁሉ ያለ ማንጐራጐርና ያለ መጠራጠር በፍቅርና በስምምነት ሥሩ።

[15] እንደ እግዚአብሔር ልጆች ንጹሓንና የዋሃን ትሆኑ ዘንድ፥ በማያምኑና በጠማሞች ልጆች መካከል ነውር ሳይኖርባችሁ በዓለም እንደ ብርሃን ትታያላችሁ፤

[16] የሕይወትን ቃል እያስተማራችሁ፤ ክርስቶስ በሚመጣበት ቀን እኔ እንድመካ፤ የሮጥሁ በከንቱ አይደለምና፤ የደከምሁም በከንቱ አይደለምና።

[17] ስለ ሃይማኖታችሁም የአምልኮ መሥዋዕትን እሠዋለሁ። እነሆም እኔ በእናንተ ደስ ይለኛል፤

[18] እናንተም በእኔ ደስ ይበላችሁ። ከእኔም ጋር ሐሤት አድርጉ።

[19] ጢሞቴዎስን እንድልክላችሁ፥ እኔም ዜናችሁን ሰምቼ ደስ እንዲለኝ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ተስፋ አደርጋለሁ።

[20] ከእርሱ በቀር፥ እንደ እኔ ሆኖ በማስተዋል ግዳጃችሁን የሚፈጽም የለኝምና።

[21] የክርስቶስን ያይደለ፥ ሁሉም የራሱን ጉዳይ ያስባልና።

[22] ልጅ አባቱን እንደሚያገለግል፥ በወንጌል ትምህርት እንደ አገለገለኝ፥ የዚህን ሰው ጠባዩን ታውቃላችሁ።

[23] እንግዲህ እንዴት እንደ አለሁ በዐወቅሁ ጊዜ፥ እርሱን በቶሎ እንደምልከው ተስፋ አደርጋለሁ፤

[24] እኔም ፈጥኜ እንደምመጣ በጌታችን አምናለሁ።

[25] አሁንም አብሮኝ የሚሠራውን ወንድማችንን አፍሮዲጡን ወደ እናንተ ልልከው አስቤአለሁ፤ እርሱም የክርስቶስ ሎሌ ነው፤ ለእናንተም መምህራችሁ ነው፤ ለእኔም ለችግሬ ጊዜ መልእክተኛዬ ነው።

[26] እንደ ታመመ፥ ለሞትም እንደ ደረሰ መስማታችሁን ዐውቆ ሊያያችሁ ይሻልና።

[27] ነገር ግን እግዚአብሔር ማረው፤ በኀዘን ላይ ኀዘን እንዳይጨመርብኝ ለእኔም እንጂ ለእሱ ብቻ አይደለም።

[28] እንድታዩትና ደስ እንዲላችሁ፥ እኔም እንዳላዝን በቶሎ እልከዋለሁ።

[29] እንግዲህ በጌታችን በፍጹም ደስታ ተቀበሉት፤ እንደዚህ ያሉትንም ሁሉ አክብሩአቸው።

[30] የእግዚአብሔርን ሥራ ስለ መሥራት እስከ ሞት ደርሶአልና፥ ከእኔ መልእክትም እናንተ ያጐደላችሁትን ይፈጽም ዘንድ ሰውነቱን አሳልፎ ሰጥቶአልና።

ወደ ፊልጵስዩስ ሰዎች። — Chapters