[1] አሁንም ወንድሞቼ ሆይ፥ በጌታችን ደስ ይበላችሁ፤ እኔም ስጽፍላችሁ ቸል አልልም፤ ያበረታችኋልና።
[2] ከውሾች ተጠበቁ፤ ከክፉ አድራጊዎችም ተጠበቁ፤ ሥጋቸውን ብቻ በመቐረጥ ተገዝረናል ከሚሉም ተጠበቁ።
[3] ግዙራንስ እግዚአብሔርን በመንፈስ የምናገለግለውና የምናመልከው እኛ ነን፤ እኛም በኢየሱስ ክርስቶስ እንመካለን እንጂ በሥጋችን የምንመካ አይደለም።
[4] እኔም ግዝረት ሳለኝ በግዝረት አልመካም፤ በግዝረት መመካትን የሚያስብ ካለም እኔ እርሱን እበልጠዋለሁ።
[5] በስምንተኛው ቀን የተገዘርሁ፥ ከእስራኤል ሕዝብ ከብንያም ነገድ ከዕብራውያን ዕብራዊ ነኝ፤ በኦሪትም ፈሪሳዊ ነበርሁ።
[6] በኦሪት ጽድቅም ያለ ነውር ሆኜ በቅንዐት ምእመናንን አሳድድ ነበር።
[7] ነገር ግን ስለ ክርስቶስ ያን ጥቅሜን ላጣው ወደድሁ።
[8] ክርስቶስን አገለግለው ዘንድ፥ ሁሉን የተውሁለት፥ እንደ ጕuድፍም ያደረግሁለት የጌታዬን የኢየሱስ ክርስቶስን ኀይልና ገናናነት ስለማውቅ ሁሉን እንደ ኢምንት ቈጠርሁት።
[9] በእርሱም እጸና ዘንድ፥ ዛሬ የኦሪት ጽድቅ ሳይኖረኝ ክርስቶስን በማመን ከእግዚአብሔር የሚገኝ ጽድቅ አለኝ እንጂ።
[10] በእርሱም ኢየሱስ ክርስቶስን አውቀዋለሁ፤ የመነሣቱንም ኀይል በሕማሙ እሳተፈዋለሁ፤ በሞቱም እመስለዋለሁ።
[11] ይኸውም ሙታን በሚነሡ ጊዜ ምናልባት በዚህ አገኘው እንደ ሆነ ብዬ ነው።
[12] ነገር ግን ይህን ፈጽሜ የተቀበልሁ አይደለም፤ ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ እርሱ እኔን የመረጠበትን አገኝ ዘንድ እሮጣለሁ እንጂ።
[13] ወንድሞቼ ሆይ፥ እኔ ግን ፍጻሜዬን ገና ያገኘሁ አይመስለኝም።
[14] የኋላዬን እረሳለሁና፥ ወደ ፊቴም ፈጥኜ እገሠግሣለሁና፤ በኢየሱስ ክርስቶስም ከፍ ከፍ ያለውን የእግዚአብሔርን የጥሪ ዋጋ ለማግኘት ወደ ግቡ እፈጥናለሁ።
[15] ፍጹማን የሆናችሁ ሁላችሁ ይህን አስቡ፤ ሌላ የምታስቡት ቢኖርም፥ እርሱን እግዚአብሔር ይገልጥላችኋል።
[16] ነገር ግን በደረስንበት ሥራ በአንድነት እንበርታ።
[17] ወንድሞቼ ሆይ፥ እኔን ምሰሉ፤ እንዲህ ባለ መንገድ የሚሄዱትንም እኛን ታዩ እንደ ነበረበት ጊዜ ተጠባበቌቸው።
[18] ዘወትር እንደምነግራችሁ፥ ልዩ አካሄድ የሚሄዱ ብዙዎች አሉና፤ አሁንም እነርሱ የክርስቶስ የመስቀሉ ጠላቶች እንደ ሆኑ በግልጥ እያለቀስሁ እነግራችኋለሁ።
[19] እነዚህም ፍጻሜያቸው ለጥፋት የሆነ፥ ሆዳቸውን የሚያመልኩ፥ ክብራቸውም ውርደት የሆነባቸው፥ ምድራዊዉንም የሚያስቡ ናቸው።
[20] እኛስ ሀገራችን በሰማይ ያለችው ናት፤ ከዚያም እርሱን ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን እንጠባበቃለን።
[21] እርሱም እንደ ከሃሊነቱ ረዳትነት መጠን የተዋረደውን ሥጋችንን የሚያድሰው፥ ክቡር ሥጋዉንም እንዲመስል የሚያደርገው፥ የሚያስመስለውም፥ ሁሉም የሚገዛለት ነው።