Skip to content
Opens in a new window
Listen to this chapter • 3:38

[1] ወንድሞቻችን ሆይ፥ ያደረግንላችሁን እናንተ ራሳችሁ ታውቃላችሁ፤ ወደ እናንተ መግባታችንም በከንቱ አይደለም።

[2] እንደምታውቁትም በፊልጵስዩስ መከራ ተቀበልን፤ ተሰደብን፤ ያንጊዜም በአምላካችን ደፍረን፥ የክርስቶስን ወንጌል በብዙ ገድል አስተማርናችሁ።

[3] ትምህርታችን የስሕተትና የርኵuሰት፥ የሽንገላም አይደለምና፤

[4] ነገር ግን እግዚአብሔር ስለ ፈተነንና ወንጌሉን ለማስተማር የታመን ስለ አደረገን እንዲህ እናስተምራለን፤ ሰውን ደስ ለማሰኘት እንደሚሠራም አይደለም፤ ልቡናችንን ለመረመረው ለእግዚአብሔር ነው እንጂ።

[5] ከሆነም ጀምሮ እንደምታውቁት በቃል አልሸነገልናችሁም፤ በምክንያትም አልቀማናችሁም፤ በዚህም እግዚአብሔር ምስክራችን ነው።

[6] የክርስቶስ ሐዋርያት እንደ መሆናችን ልናከብድባችሁ ሲቻለን ከእናንተም ቢሆን፥ ከሌላም ቢሆን ከሰው ክብርን አንፈልግም።

[7] ነገር ግን በመካከላችሁ እንደ ሕፃናትና ልጆችዋን እንደምታሳድግ እንደ ሞግዚት ሆንን፤ ከሰው ክብርን አንፈልግም።

[8] እኛም እንዲሁ እንወዳችኋለን፤ የእግዚአብሔርን ወንጌል ብቻ ሳይሆን፥ ሰውነታችንንም ጭምር ልንሰጣችሁ እናስብላችኋለን፤ ወዳጆች ሆናችሁናልና።

[9] ወንድሞቻችን ሆይ፥ ድካማችንንና ጥረታችንን አስቡ፤ ከእናንተ በአንዱ ስንኳ እንዳንከብድበት በቀንና በሌሊት እየሠራን የእግዚአብሔርን ወንጌል ሰበክንላችሁ።

[10] በምታምኑት በእናንተ ሁሉ ዘንድ በእውነትና በቅንነት፥ በንጽሕናም እንደ ሄድን እናንተ ራሳችሁ ምስክሮቻችን ናችሁ፤ እግዚአብሔርም ምስክር ነው።

[11] ከእናንተ እያንዳንዳችሁ እንደምታውቁት፥ አባት ለልጁ እንደሚያደርግ እንማልዳችኋለን፤ እናረጋጋችኋለንም።

[12] ወደ ጌትነቱ መንግሥት ወደ ጠራችሁ እግዚአብሔር በሚገባችሁ ትሄዱ ዘንድ እናዳኝባችኋለን።

[13] ስለዚህም እኛ ዘወትር እግዚአብሔርን እናመሰግነዋለን፤ ከእኛ የሰማችሁትን እግዚአብሔር ያዘዘውን ቃል ተቀብላችኋልና፤ የሰውንም ቃል አይደለም፤ ነገር ግን ያመናችሁትን እናንተን በሥራ የሚረዳችሁ በእውነት የእግዚአብሔር ቃል ነው።

[14] እናንተም ወንድሞቻችን፥ በኢየሱስ ክርስቶስ አምነው፥ በይሁዳ ያሉትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን መሰላችሁ፤ እነርሱ ከአይሁድ መከራን እንደ ተቀበሉ፥ እናንተም ከወገኖቻችሁ መከራን ተቀብላችኋልና።

[15] እነርሱም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን የገደሉት ናቸው፤ በመካከላቸው የነበሩ ነቢያትንም፥ እኛንም አሳደዱ፤ እግዚአብሔርንም ደስ አያሰኙትም፤ ከሰው ሁሉ ጋርም ይጣላሉ።

[16] ኀጢአታቸው አዘውትሮ ይፈጸምባቸው ዘንድ፥ ለአሕዛብ የሚድኑበትን እንዳንነግራቸው ይከለክሉናል፤ እነሆ፥ ለዘለዓለም የሚሆን መቅሠፍታቸውም ደረሰባቸው።

[17] ወንድሞቻችን ሆይ፥ እኛስ በዚህ ወራት ከእናንተ የተነሣ እንደ ሙት ልጅ ሆን፤ ከፊት ነው እንጂ ከልብ አይደለም፤ ፊታችሁንም ልናይ እጅግ ናፍቀናል።

[18] እኔ ጳውሎስ አንድ ጊዜና ሁለት ጊዜ ወደ እናንተ ልመጣ ብዙ ወደድሁ፤ ነገር ግን ሰይጣን አሰናከለኝ።

[19] አለኝታችንና ደስታችን፥ የትምክሕታችን አክሊልስ ማን ነው? በሚመጣበት ጊዜ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ፊት እናንተ አይደላችሁምን?

[20] ክብራችንና ደስታችን እናንተ ናችሁና።

ወደ ተሰሎንቄ ሰዎች 1 — Chapters