Skip to content
Opens in a new window
Listen to this chapter • 2:01

[1] ከጳውሎስና ከስልዋኖስ፥ ከጢሞቴዎስም፥ በአባታችን በእግዚአብሔር፥ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስም ላመኑ በተሰሎንቄ ላሉ ማኅበረ ክርስቲያን፤ ከአባታችን ከእግዚአብሔርና ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ሰላምና ጸጋ ለእናንተ ይሁን።

[2] ስለ እናንተ ዘወትር እግዚአብሔርን እናመሰግነዋለን፤ ሁልጊዜም በጸሎታችን ሳናቌርጥ እናስባችኋለን።

[3] በአባታችን በእግዚአብሔር ፊት የሃይማኖታችሁን ሥራና የፍቅራችሁን ጽናት፥ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ የሚሆን የተስፋችሁንም ትዕግሥት እናስባለን።

[4] የተወደዳችሁ ወንድሞቻችን ሆይ፥ እግዚአብሔር እንደ መረጣችሁ እናውቃለን።

[5] የወንጌል ትምህርታችን በኀይልና በመንፈስ ቅዱስ፥ በታመነ ምልጃም እንጂ፥ በእናንተ ዘንድ በቃል ብቻ አይደለምና፤ ስለ እናንተም በእናንተ ዘንድ የሆነውን እናንተ ታውቃላችሁ።

[6] እነሆ፥ እናንተም እኛንና ጌታን መሰላችሁ፤ በብዙ መከራ ከመንፈስ ቅዱስ ደስታ ጋር ቃሉን ተቀብላችኋልና።

[7] በመቄዶንያና በአካይያ ላሉ ምእመናን ሁሉ ምሳሌ ሆናችኋል።

[8] የጌታችንን ቃል ከእናንተ ሰምተው ተምረዋልና፤ ነገር ግን በመቄዶንያና በአካይያ ብቻ አይደለም፤ ደግሞም በእግዚአብሔር ማመናችሁ በያገሩ ተሰምታለች፤ እኛም ስለ እናንተ ምንም ልንናገር አንሻም።

[9] እኛ ወደ እናንተ እንደ መጣን፥ እናንተም ለሕያውና ለእውነተኛ አምላክ ታገለግሉ ዘንድ፥ ከጣዖት አምልኮ ወደ እግዚአብሔር እንደ ተመለሳችሁ እነርሱ ራሳቸው ያውቃሉ።

[10] ከሙታን ተለይቶ የተነሣ ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስን ከሰማያት ተስፋ እያደረጋችሁ፥ እርሱም ከሚመጣው መከራ ያድነናል።

ወደ ተሰሎንቄ ሰዎች 1 — Chapters