[1] -
[2] እንዳይፈረድባችሁ አትፍረዱ፤ በምትፈርዱበት ፍርድ ይፈረድባችኋልና፥ በምትሰፍሩበትም መስፈሪያ ይሰፈርባችኋል።
[3] በወንድምህም ዓይን ያለውን ጉድፍ ስለምን ታያለህ፥ በዓይንህ ግን ያለውን ምሰሶ ስለ ምን አትመለከትም?
[4] ወይም ወንድምህን። ከዓይንህ ጉድፍ ላውጣ ፍቀድልኝ እንዴትስ ትለዋለህ? እነሆም፥ በዓይንህ ምሰሶ አለ።
[5] አንተ ግብዝ፥ አስቀድመህ ከዓይንህ ምሰሶውን አውጣ፥ ከዚያም በኋላ ከወንድምህ ዓይን ጉድፉን ታወጣ ዘንድ አጥርተህ ታያለህ።
[6] በእግራቸው እንዳይረግጡት ተመልሰውም እንዳይነክሱአችሁ፥ የተቀደሰውን ለውሾች አትስጡ፥ ዕንቁዎቻችሁንም በእሪያዎች ፊት አትጣሉ።
[7] ለምኑ፥ ይሰጣችሁማል፤ ፈልጉ፥ ታገኙማላችሁ፤ መዝጊያን አንኳኩ፥ ይከፈትላችሁማል።
[8] የሚለምነው ሁሉ ይቀበላልና፥ የሚፈልገውም ያገኛል፥ መዝጊያንም ለሚያንኳኳ ይከፈትለታል።
[9] ወይስ ከእናንተ፥ ልጁ እንጀራ ቢለምነው፥ ድንጋይን የሚሰጠው ከእናንተ ማን ሰው ነው?
[10] ዓሣስ ቢለምነው እባብን ይሰጠዋልን?
[11] እንኪያስ እናንተ ክፉዎች ስትሆኑ ለልጆቻችሁ መልካም ስጦታ መስጠትን ካወቃችሁ፥ በሰማያት ያለው አባታችሁ ለሚለምኑት እንዴት አብልጦ መልካም ነገርን ይሰጣቸው?
[12] እንግዲህ ሰዎች ሊያደርጉላችሁ የምትወዱትን ሁሉ እናንተ ደግሞ እንዲሁ አድርጉላቸው፤ ሕግም ነቢያትም ይህ ነውና።
[13] በጠበበው ደጅ ግቡ፤ ወደ ጥፋት የሚወስደው ደጅ ሰፊ፥ መንገዱም ትልቅ ነውና፥ ወደ እርሱም የሚገቡ ብዙዎች ናቸው፤
[14] ወደ ሕይወት የሚወስደው ደጅ የጠበበ፥ መንገዱም የቀጠነ ነውና፥ የሚያገኙትም ጥቂቶች ናቸው።
[15] የበግ ለምድ ለብሰው ከሚመጡባችሁ በውሥጣቸው ግን ነጣቂዎች ተኵላዎች ከሆኑ ከሐሰተኞች ነቢያት ተጠንቀቁ።
[16] ከፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ። ከእሾህ ወይን ከኩርንችትስ በለስ ይለቀማልን?
[17] እንዲሁ መልካም ዛፍ ሁሉ መልካም ፍሬ ያደርጋል፥ ክፉም ዛፍ ክፉ ፍሬ ያደርጋል።
[18] መልካም ዛፍ ክፉ ፍሬ ማፍራት፥ ወይም ክፉ ዛፍ መልካም ፍሬ ማፍራት አይቻለውም።
[19] መልካም ፍሬ የማያደርግ ዛፍ ሁሉ ይቆረጣል ወደ እሳትም ይጣላል።
[20] ስለዚህም ከፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ።
[21] በሰማያት ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ እንጂ፥ ጌታ ሆይ፥ ጌታ ሆይ፥ የሚለኝ ሁሉ መንግሥተ ሰማያት የሚገባ አይደለም።
[22] በዚያ ቀን ብዙዎች። ጌታ ሆይ፥ ጌታ ሆይ፥ በስምህ ትንቢት አልተናገርንምን፥ በስምህስ አጋንንትን አላወጣንምን፥ በስምህስ ብዙ ተአምራትን አላደረግንምን? ይሉኛል።
[23] የዚያን ጊዜም። ከቶ አላወቅኋችሁም፤ እናንተ ዓመፀኞች፥ ከእኔ ራቁ ብዬ እመሰክርባቸዋለሁ።
[24] ስለዚህ ይህን ቃሌን ሰምቶ የሚያደርገው ሁሉ ቤቱን በዓለት ላይ የሠራ ልባም ሰውን ይመስላል።
[25] ዝናብም ወረደ ጎርፍም መጣ ነፋስም ነፈሰ ያንም ቤት ገፋው፥ በዓለት ላይም ስለ ተመሠረተ አልወደቀም።
[26] ይህንም ቃሌን ሰምቶ የማያደርገው ሰው ሁሉ ቤቱን በአሸዋ ላይ የሠራ ሰነፍ ሰውን ይመስላል።
[27] ዝናብም ወረደ ጎርፍም መጣ ነፋስም ነፈሰ ያንም ቤት መታው፥ ወደቀም፥ አወዳደቁም ታላቅ ሆነ።
[28] ኢየሱስም ይህን ነገር በጨረሰ ጊዜ ሕዝቡ በትምህርቱ ተገረሙ፤ እንደ ጻፎቻቸው ሳይሆን
[29] እንደ ባለ ሥልጣን ያስተምራቸው ነበርና።