[1] ኢየሱስም መለሰ ደግሞም በምሳሌ ነገራቸው እንዲህም አለ።
[2] መንግሥተ ሰማያት ለልጁ ሰርግ ያደረገ ንጉሥን ትመስላለች።
[3] የታደሙትንም ወደ ሰርጉ ይጠሩ ዘንድ ባሮቹን ላከ ሊመጡም አልወደዱም።
[4] ደግሞ ሌሎችን ባሮች ልኮ። የታደሙትን። እነሆ፥ ድግሴን አዘጋጀሁ፥ ኮርማዎቼና የሰቡት ከብቶቼ ታርደዋል፥ ሁሉም ተዘጋጅቶአል፤ ወደ ሰርጉ ኑ በሉአቸው አለ።
[5] እነርሱ ግን ቸል ብለው አንዱ ወደ እርሻው፥ ሌላውም ወደ ንግዱ ሄደ፤
[6] የቀሩትም ባሮቹን ይዘው አንገላቱአቸው ገደሉአቸውም።
[7] ንጉሡም ተቈጣ፥ ጭፍሮቹንም ልኮ እነዚያን ገዳዮች አጠፋ፤ ከተማቸውንም አቃጠለ።
[8] በዚያን ጊዜ ባሮቹን። ሰርጉስ ተዘጋጅቶአል፥ ነገር ግን የታደሙት የማይገባቸው ሆኑ፤
[9] እንግዲህ ወደ መንገድ መተላለፊያ ሄዳችሁ ያገኛችሁትን ሁሉ ወደ ሰርጉ ጥሩ አለ።
[10] እነዚያም ባሮች ወደ መንገድ ወጥተው ያገኙትን ሁሉ ክፉዎችንም በጎዎችንም ሰበሰቡ፤ የሰርጉንም ቤት ተቀማጮች ሞሉት።
[11] ንጉሡም የተቀመጡትን ለማየት በገባ ጊዜ በዚያ የሰርግ ልብስ ያለበሰ አንድ ሰው አየና። ወዳጄ ሆይ፥
[12] የሰርግ ልብስ ሳትለብስ እንዴት ወደዚህ ገባህ? አለው እርሱም ዝም አለ።
[13] በዚያን ጊዜ ንጉሡ አገልጋዮቹን። እጁንና እግሩን አስራችሁ በውጭ ወዳለው ጨለማ አውጡት፤ በዚያ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል አለ።
[14] የተጠሩ ብዙዎች፥ የተመረጡ ግን ጥቂቶች ናቸውና።
[15] ስለዚህ ፈሪሳውያን ሄዱና እንዴት አድርገው በነገር እንዲያጠምዱት ተማከሩ።
[16] ደቀ መዛሙርታቸውንም ከሄሮድስ ወገን ጋር ላኩበት፥ እነርሱም። መምህር ሆይ፥ እውነተኛ እንደ ሆንህ በእውነትም የእግዚአብሔርን መንገድ እንድታስተምር እናውቃለን፥ ለማንምም አታደላም፥ የሰውን ፊት አትመለከትምና፤
[17] እንግዲህ ምን ይመስልሃል? ንገረን ለቄሣር ግብር መስጠት ተፈቅዶአልን ወይስ አልተፈቀደም? አሉት።
[18] ኢየሱስም ክፋታቸውን አውቆ። እናንተ ግብዞች፥ ስለ ምን ትፈትኑኛላችሁ?
[19] የግብሩን ብር አሳዩኝ አለ። እነርሱም ዲናር አመጡለት።
[20] እርሱም። ይህች መልክ ጽሕፈቲቱስ የማን ናት? አላቸው።
[21] የቄሣር ነው አሉት። በዚያን ጊዜ። እንኪያስ የቄሣርን ለቄሣር የእግዚአብሔርንም ለእግዚአብሔር አስረክቡ አላቸው።
[22] ይህንም ሰምተው ተደነቁ፥ ትተውትም ሄዱ።
[23] በዚያን ቀን። ትንሣኤ ሙታን የለም የሚሉ ሰዱቃውያን ወደ እርሱ ቀረቡ፥
[24] እንዲህም ብለው ጠየቁት። መምህር ሆይ፥ ሙሴ አንድ ሰው ልጅ ሳይወልድ ሲሞት ወንድሙ ሚስቱን አግብቶ ለወንድሙ ዘር ይተካ አለ።
[25] ሰባት ወንድማማች በእኛ ዘንድ ነበሩ፤ ፊተኛውም ሚስት አግብቶ ሞተ፥ ዘርም ስለሌለው ሚስቱን ለወንድሙ ተወለት፤
[26] እንዲሁ ደግሞ ሁለተኛው ሦስተኛውም፥ እስከ ሰባተኛው ድረስ።
[27] ከሁሉም በኋላ ሴቲቱ ሞተች።
[28] ሁሉ አግብተዋታልና በትንሣኤ ቀንስ፥ ከሰባቱ ለማናቸው ሚስት ትሆናለች?
[29] ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው። መጻሕፍትንና የእግዚአብሔርን ኃይል አታውቁምና ትስታላችሁ።
[30] በትንሣኤስ እንደ እግዚአብሔር መላእክት በሰማይ ይሆናሉ እንጂ አያገቡም አይጋቡምም።
[31] -
[32] ስለ ትንሣኤ ሙታን ግን። እኔ የአብርሃም አምላክ፥ የይስሐቅም አምላክ የያዕቆብም አምላክ ነኝ የሚል ከእግዚአብሔር ዘንድ ወደ እናንተ የተባለውን አላነበባችሁምን? የሕያዋን አምላክ ነው እንጂ የሙታን አይደለም።
[33] ሕዝቡም ይህን ሰምተው በትምህርቱ ተገረሙ።
[34] ፈሪሳውያንም ሰዱቃውያንን ዝም እንዳሰኛቸው በሰሙ ጊዜ አብረው ተሰበሰቡ።
[35] ከእነርሱም አንድ ሕግ አዋቂ ሊፈትነው።
[36] መምህር ሆይ፥ ከሕግ ማናቸይቱ ትእዛዝ ታላቅ ናት? ብሎ ጠየቀው።
[37] ኢየሱስም እንዲህ አለው። ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ በፍጹም ነፍስህም በፍጹም አሳብህም ውደድ።
[38] ታላቂቱና ፊተኛይቱ ትእዛዝ ይህች ናት።
[39] ሁለተኛይቱም ይህችን ትመስላለች፥ እርስዋም። ባልንጀራህን እንደ ነፍስህ ውደድ የምትለው ናት።
[40] በእነዚህ በሁለቱ ትእዛዛት ሕጉም ሁሉ ነቢያትም ተሰቅለዋል።
[41] -
[42] ፈሪሳውያንም ተሰብስበው ሳሉ፥ ኢየሱስ። ስለ ክርስቶስ ምን ይመስላችኋል? የማንስ ልጅ ነው? ብሎ ጠየቃቸው። የዳዊት ልጅ ነው አሉት።
[43] -
[44] እርሱም። እንኪያስ ዳዊት። ጌታ ጌታዬን። ጠላቶችህን የእግርህ መረገጫ እስካደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ አለው ሲል እንዴት በመንፈስ ጌታ ብሎ ይጠራዋል?
[45] ዳዊትስ ጌታ ብሎ ከጠራው፥ እንዴት ልጁ ይሆናል? አላቸው።
[46] አንድም ቃል ስንኳ ይመልስለት ዘንድ የተቻለው የለም፥ ከዚያ ቀንም ጀምሮ ወደ ፊት ማንም ሊጠይቀው አልደፈረም።