[1] -
[2] በዚያም ወራት መጥምቁ ዮሐንስ። መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ ብሎ በይሁዳ ምድረ በዳ እየሰበከ መጣ።
[3] በነቢዩ በኢሳይያስ። የጌታን መንገድ አዘጋጁ ጥርጊያውንም አቅኑ እያለ በምድረ በዳ የሚጮህ ሰው ድምፅ የተባለለት ይህ ነውና።
[4] ራሱም ዮሐንስ የግመል ጠጉር ልብስ ነበረው፥ በወገቡም ጠፍር ይታጠቅ ነበር፤ ምግቡም አንበጣና የበረሀ ማር ነበረ።
[5] ያን ጊዜ ኢየሩሳሌም ይሁዳም ሁሉ በዮርዳኖስም ዙሪያ ያለ አገር ሁሉ ወደ እርሱ ይወጡ ነበር፤
[6] ኃጢአታቸውንም እየተናዘዙ በዮርዳኖስ ወንዝ ከእርሱ ይጠመቁ ነበር።
[7] ዳሩ ግን ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን ብዙዎች ወደ ጥምቀቱ ሲመጡ ባየ ጊዜ፥ እንዲህ አላቸው። እናንተ የእፉኝት ልጆች፥ ከሚመጣው ቍጣ እንድትሸሹ ማን አመለከታችሁ?
[8] እንግዲህ ለንስሐ የሚገባ ፍሬ አድርጉ፤
[9] በልባችሁም። አብርሃም አባት አለን እንደምትሉ አይምሰላችሁ፤ እላችኋለሁና። ከነዚህ ድንጋዮች ለአብርሃም ልጆች ሊያስነሣለት እግዚአብሔር ይችላል።
[10] አሁንስ ምሳር በዛፎች ሥር ተቀምጦአል፤ እንግዲህ መልካም ፍሬ የማያደርግ ዛፍ ሁሉ ይቈረጣል ወደ እሳትም ይጣላል።
[11] እኔስ ለንስሐ በውኃ አጠምቃችኋለሁ፤ ጫማውን እሸከም ዘንድ የማይገባኝ ከእኔ በኋላ የሚመጣው ግን ከእኔ ይልቅ ይበረታል፤ እርሱ በመንፈስ ቅዱስ በእሳትም ያጠምቃችኋል፤
[12] መንሹም በእጁ ነው፥ አውድማውንም ፈጽሞ ያጠራል፥ ስንዴውንም በጎተራው ይከታል፥ ገለባውን ግን በማይጠፋ እሳት ያቃጥለዋል።
[13] ያን ጊዜ ኢየሱስ በዮሐንስ ሊጠመቅ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ መጣ።
[14] ዮሐንስ ግን። እኔ በአንተ ልጠመቅ ያስፈልገኛል አንተም ወደ እኔ ትመጣለህን? ብሎ ይከለክለው ነበር።
[15] ኢየሱስም መልሶ። አሁንስ ፍቀድልኝ፤ እንዲህ ጽድቅን ሁሉ መፈጸም ይገባናልና አለው። ያን ጊዜ ፈቀደለት።
[16] ኢየሱስም ከተጠመቀ በኋላ ወዲያው ከውኃ ወጣ፤ እነሆም፥ ሰማያት ተከፈቱ የእግዚአብሔርም መንፈስ እንደ ርግብ ሲወርድ በእርሱ ላይም ሲመጣ አየ፤
[17] እነሆም፥ ድምፅ ከሰማያት መጥቶ። በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው አለ።