Skip to content
Opens in a new window
Listen to this chapter • 3:43

[1] አምስተኛውም መልአክ መለከቱን በነፋ ጊዜ፥ ኮከብ ከሰማይ ወደ ምድር ሲወድቅ አየሁ፤ ለእርሱም የጥልቁ ምንጭ መክፈቻ ተሰጠው።

[2] የጥልቁንም ምንጭ ከፈተ፤ ጢስም እንደ ታላቅ ምድጃ ጢስ ሆኖ ከጥልቁ ወጣ፤ ፀሓይና አየርም ከጥልቁ በወጣው ጢስ ጨለሙ።

[3] ከጢሱም አንበጣዎች ወደ ምድር ወጡ፤ እንደ ምድር ጊንጦችም ሥልጣን ተሰጣቸው።

[4] በግንባራቸውም የእግዚአብሔር ማሕተም ከሌለባቸው ሰዎች በቀር፥ በምድር ያለውን ሣሩንና ቅጠሉን፥ ዛፉንም እንዳያጠፉ ታዘዙ።

[5] አምስት ወርም መከራ እንዲያጸኑባቸው እንጂ እንዳይገድሏቸው ታዘዙ፤ ሕመማቸው ግን፥ ጊንጥ ሰውን ነድፎ እንደሚያሠቃይ ነው።

[6] በእነዚያ ቀኖችም ሰው ሞትን ይሻል፤ አያገኝምም፤ ሊሞት ይመኛል፤ ሞትም ከእርሱ ይሸሻል።

[7] የአንበጦችም መልካቸው እንዲህ ነው፥ ለጦርነት እንደ ተዘጋጁ ፈረሶች ይመስላሉ፤ በራሳቸውም ላይ በወርቅ አምሳል የተሠራ አክሊል ነበራቸው፤ ፊታቸውም እንደ ሰው ፊት ነበረ።

[8] ጠጕuራቸውም እንደ ሴቶች ጠጕuር ነበረ፤ ጥርሳቸውም እንደ አንበሳ ጥርስ ነበረ።

[9] የብረት ጥሩር የሚመስልም ጥሩር ነበራቸው፤ የክንፋቸውም ድምፅ ወደ ጦርነት እንደሚጋልቡ እንደ ብዙ ፈረሶች ሠረገላ ድምፅ ነበረ።

[10] እንደ ጊንጥ ጅራትም ያለ ጅራት አላቸው፤ በጅራታቸውም መውጊያ አለ፤ ሰዎችንም አምስት ወር እንዲወጉበት ሥልጣን አላቸው።

[11] በእነርሱም ላይ የጥልቅ መልአክ ንጉሥ አላቸው፤ ስሙም በዕብራይስጥ አብዶን፥ በጽርዕ አጵልዮን ይባላል።

[12] በዚህም አንዲቱ መከራ አልፋለች፥ ገና ሁለት መከራ ይመጣል።

[13] ስድስተኛውም መልአክ መለከቱን በነፋ ጊዜ በእግዚአብሔር ፊት ካለው ከወርቁ መሠዊያ ቀንዶች አንድ ድምፅ ሰማሁ።

[14] መለከት የያዘውን ስድስተኛውንም መልአክ ፥ “በታላቁ በኤፍራጥስ ወንዝ የታሠሩትን እነዚያን አራቱን መላእክት ፍታቸው ” አለው።

[15] ያንጊዜም ለሰዓቱና ለዕለቱ፥ ለወሩና ለዓመቱ የተዘጋጁት እነዚያ አራቱ መላእክት የሰዎችን ሲሶ ይገድሉ ዘንድ ተፈቱ።

[16] የፈረሰኟቹም ጭፍራ ቐጥር እልፍ ጊዜ እልፍና እልፍ ጊዜ እልፍ ነበረ። ቐጥራቸውንም ሰማሁ።

[17] ፈረሶቹንና በእነርሱም ላይ የተቀመጡትን እንዲሁ በራእይ አየሁ፤ እሳትና ያክንት፥ ዲንም የሚመስል ጥሩር ነበራቸው፤ የፈረሶቹም ራስ እንደ አንበሳ ራስ ነበረ፤ ከአፋቸውም እሳትና ጢስ ዲንም ወጣ።

[18] ከአፋቸውም በሚወጣው በእሳቱ፥ በጢሱና በዲኑ በእነዚህ ሦስት መቅሠፍቶች የሰዎች ሲሶ ተገደለ።

[19] የፈረሶቻቸውም ሥልጣን በአፋቸውና በጅራቶቻቸው ነውና ጅራታቸው እባብን ይመስላል፤ ራስም አላቸው፤ በእርሱም ይነድፋሉ።

[20] በእነዚያም መቅሠፍቶች ያልሞቱ የቀሩት ሰዎች፥ ለአጋንንትና ያዩ፥ ወይም ይሰሙ፥ ወይም ይሄዱ፥ ዘንድ ለማይችሉ፥ ከወርቅና ከብር፥ ከናስና ከድንጋይ ከዕንጨትም ለተሠሩ ጣዖታት እንዳይሰግዱ ስለ እጃቸው ሥራ ንስሓ አልገቡም።

[21] ደግሞም ስለ መግደላቸውም ቢሆን ወይም ስለ አስማታቸው፥ ወይም ስለ ዝሙታቸው፥ ወይም ስለ ስርቆታቸው ንስሓ አልገቡም።

የዮሐንስ ራእይ። የዮሐንስ ራእይ — Chapters