Skip to content
Opens in a new window
Listen to this chapter • 3:01

[1] ከዚህም በኋላ፥ በዙፋኑ ላይ በተቀመጠው በቀኝ እጁ ላይ በውስጥና በውጭ የተጻፈባት፥ በሰባትም ማኅተም የታተመች መጽሐፍን አየሁ።

[2] ኀያል መልአክም ፥ “ያቺን መጽሐፍ ይገልጥ ዘንድ፥ ማኅተሞችንም ይፈታ ዘንድ ለማን ይገባዋል?” እያለ በታላቅ ድምፅ አሰምቶ ሲናገር አየሁ።

[3] በሰማይም ቢሆን፥ በምድርም ቢሆን፥ ከምድርም በታች ቢሆን፥ ያችን መጽሐፍ ሊገልጥና ሊያያት የተቻለው የለም።

[4] ያለቀሱ ብዙዎች ናቸው፤ እኔም አብሬአቸው አለቀስሁ፤ ያቺን መጽሐፍ ሊገልጣትና ሊያያት የሚገባው ሆኖ የተገኘ የለምና።

[5] ከአለቆቹም አንዱ ፥ “አታልቅስ፥ እነሆ፥ ከይሁዳ ነገድ የሆነው አንበሳ እርሱም የዳዊት ዘር መጽሐፉን ይገልጥ ዘንድ፥ ሰባቱንም ማኅተም ይፈታ ዘንድ፥ ድል ነሥቶአል ” አለኝ።

[6] በዙፋኑና በአራቱ እንስሶች መካከል፥ በሃያ አራቱ አለቆችም መካከል እንደ ታረደ በግ ቆሞ አየሁ፤ ሰባት ቀንዶችና ሰባት ዐይኖችም ነበሩት፤ ይኸውም በምድር ሁሉ የተላከ የእግዚአብሔር መንፈስ ነው።

[7] መጥቶም በዙፋኑ ላይ ከተቀመጠው፥ ከቀኝ እጁ ይችን መጽሐፍ ወሰዳት።

[8] መጽሐፍዋንም በወሰደ ጊዜ፥ ሃያ አራቱ አለቆችና አራቱ እንስሶች በፊቱ ወድቀው ለበጉ ሰገዱለት፤ ሁሉም በገናንና የቅዱሳን ጸሎት የሆነ ዕጣን የሞላበትን የወርቅ ዕቃ ይዘዋል።

[9] በአዲስ መዝሙርም ይዘምሩ ነበር፤ እንዲህም ይሉ ነበር ፥ “ያቺን መጽሐፍ ልትቀበል፥ ማኅተምዋንም ልትፈታ ይገባሃል፤ ተገድለሃልና፤ በደምህም ከሕዝብና ከአሕዛብ፥ ከነገድም ሁሉ፥ ከወገንም ሁሉ ሰዎችን ለእግዚአብሔር ዋጅተሃልና።

[10] ከእነርሱም፥ ለአምላካችን ነገሥታትንና ካህናትን ሾምህ፤ በምድርም ሁሉ ይነግሣሉ።”

[11] አየሁም፥ በዙፋኑም በእንስሶቹና በአለቆቹ ዙሪያ የብዙ መላእክትን ድምፅ ሰማሁ፤ ቐጥራቸውም የብዙ ብዙ እልፍ አእላፋት ነበር።

[12] በታላቅ ድምፅም እንዲህ አሉ ፥ “ለታረደው በግ ፥ ኀይልንና ባለጠግነትን፥ ጥበብንና ብርታትንም፥ ክብርንና ምስጋናንም፥ በረከትንም ሊቀበል ይገባዋል።”

[13] በሰማይና በምድር፥ ከምድርም በታች፥ በባሕርም ላይ ያለ ፍጥረት ሁሉ፥ በእነርሱም ውስጥ ያለው ሁሉ “በረከትና ክብር፥ ምስጋናና ኀይልም ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም በዙፋኑ ለተቀመጠው፥ ለበጉም ይሁን ” ሲሉ ሰማሁ።

[14] አራቱ እንስሶችም አሜን አሉ፤ እነዚያም አለቆች ወድቀው ሰገዱለት።

የዮሐንስ ራእይ። የዮሐንስ ራእይ — Chapters