Skip to content
Opens in a new window
Listen to this chapter • 5:53

[1] ዳግመኛም በባሕር ዳር ያስተምር ጀመር፤ በባሕርም ወደ ታንኳ ገብቶ እስኪቀመጥ ድረስ ብዙ ሰዎች ወደ እርሱ ተሰበሰቡ፤ ሰውም ሁሉ በባሕሩ ዳር በምድር ላይ ነበር።

[2] በምሳሌም ብዙ አስተማራቸው፤ ሲያስተምራቸውም እንዲህ አላቸው ፥

[3] “ስሙ፥ እነሆ፥ ዘሪ ሊዘራ ወጣ።

[4] ሲዘራም በመንገድ የወደቀ ዘር ነበረ፤ ወፎችም መጥተው በሉት።

[5] አፈር በሌለበት በጭንጫ ላይም የወደቀ ነበረ፤ መሬቱም ጥልቅነት አልነበረውምና ፈጥኖ በቀለ።

[6] ፀሐይም በወጣ ጊዜ ጠወለገ፤ ሥርም አልነበረውምና ደረቀ።

[7] በእሾህ መካከልም የወደቀ ዘር ነበረ፤ እሾሁም ወጣና አነቀው፤ ፍሬም አላፈራም።

[8] በመልካም ምድር ላይም የወደቀ ዘር ነበረ፤ በቀለ፤ አደገም፤ ፍሬም ሰጠ፤ አንዱም ሠላሳ፥ ሌላውም ስድሳ፥ ሌላውም መቶ አፈራ።

[9] የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ ” አለ።

[10] ብቻውንም በሆነ ጊዜ አብረውት የነበሩት ከዐሥራ ሁለቱ ደቀ መዛሙርቱ ጋር ምሳሌውን ጠየቁት።

[11] እርሱም እንዲህ አላቸው ፥ “ለእናንተ የእግዚአብሔርን መንግሥት ምስጢር ልታውቁ ተሰጥቶአችኋል፤ በውጭ ላሉት ግን፥ በምሳሌ ይሆንባቸዋል።

[12] ማየትን አይተው እንዳያውቁ፥ መስማትንም ሰምተው እንዳያስተውሉ፥ እንዳይመለሱ፥ ይቅርም እንዳልላቸው፥ ኀጢአታቸውም እንዳይሰረይላቸው።”

[13] እርሱም እንዲህ አላቸው ፥ “ይህቺን ምሳሌ አታውቁምን? እንግዲያ ምሳሌን ሁሉ እንዴት ታውቃላችሁ?

[14] ዘሪው የእግዚአብሔርን ቃል የሚዘራ ነው።

[15] ቃል በተዘራበት መንገድ ያሉም እነዚህ ናቸው፤ ቃሉን እንደ ሰሙ ያንጊዜ ሰይጣን መጥቶ የተዘራውን ቃል ከልባቸው ይወስዳል።

[16] ዳግመኛም በጭንጫ ላይ የተዘሩ፥ ቃሉን ሰምተው ፈጥነው በደስታ የሚቀበሉት ናቸው።

[17] ለጊዜው ነው እንጂ ሥር የላቸውም፤ ስለዚህም ቃል መከራ ወይም ስደት በሆነ ጊዜ ወዲያውኑ ይክዳሉ።

[18] በእሾህም መካከል የተዘሩ ቃሉን የሚሰሙ እኒህ ናቸው።

[19] የዚህ ዓለም ዐሳብና የባለጠግነት ማታለል፥ ሌላውም ምኟት ሁሉ ይገቡበትና ቃሉን ያንቁታል፤ እርሱም አያፈራም።

[20] በመልካም ምድር የተዘሩ ቃሉን ሰምተው የሚቀበሉት ናቸው፤ አንዱ ሠላሳ፥ አንዱም ስድሳ፥ አንዱም መቶ ቅንጣት የሚያፈሩ እነዚህ ናቸው።

[21] እንዲህም አላቸው ፥ “መብራትን አብርተው እንቅብ ሊደፉባት ወይም ከአልጋ በታች ሊያኖሩአት የሚያመጡኣት አሉን? በመቅረዝዋ ላይ ሊያኖሩአት አይደለምን?

[22] የሚሸሸግ ስውር የለም፤ የማይገለጥም የተሸፈነ የለም።

[23] የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ።”

[24] እንዲህም አላቸው ፥ “የምትሰሙትን አስተውሉ፤ በሰፈራችሁበት በዚያ መስፈሪያ ይሰፍሩላችኋል፤ ይጨምሩላችኋልም።

[25] ላለው ይሰጡታል፤ ይጨምሩለታልም፤ የሌለውን ግን፤ ያን ያለውን እንኳ ይወስዱበታል።”

[26] እርሱም እንዲህ አላቸው ፥ “የእግዚአብሔር መንግሥት መልካም ዘርን በምድሩ ላይ እንደሚዘራ ሰው እንደዚሁ ናት።

[27] እርሱም በሌሊት ይተኛል፤ በመዐልትም ይነሣል፤ እርሱም ሳያውቅ ዘሩ ይበቅላል፤ ያድጋልም፤

[28] ምድሪቱም ከእርስዋ ፍሬ ትሰጣለች፤ መጀመሪያ ቡቃያን፥ ከዚህም በኋላ ዛላን፥ ቀጥሎም በዛላው ላይ ፍጹም ሰብልን ትሰጣለች።

[29] ፍሬንም ፈጽሞ ባፈራ ጊዜ ያንጊዜ መከር ደርሶአልና፤ ማጭድ ይላካል።”

[30] እንዲህም አለ ፥ “የእግዚአብሔርን መንግሥት በምን እመስላታለሁ? ምንስ ትመስላለች?

[31] እንደ ሰናፍጭ ቅንጣት ናት፤ እርስዋም በምድር በተዘራች ጊዜ በምድር ካሉ አዝርዕት ሁሉ ታንሳለች።

[32] በተዘራችም ጊዜ ትበቅላለች፤ ከአትክልትም ሁሉ ትበልጣለች፤ የሰማይ ወፎችም በቅርንጫፎችዋ በታች ሊጠለሉ እስከሚችሉ ድረስ ታላላቅ ቅርንጫፎችን ታወጣለች።”

[33] መስማትን በሚችሉበት መጠን እንዲህ ባለ ብዙ ምሳሌ ቃሉን ነገራቸው።

[34] ያለ ምሳሌ ግን አልነገራቸውም። ለብቻቸውም ሲሆኑ ለደቀ መዝሙርቱ ሁሉን ነገር ይተረጒምላቸው ነበር።

[35] ያንጊዜም ሲመሽ ደቀ መዛሙርቱን ፥ “ወደ ማዶ እንሻገር ” አላቸው።

[36] ሕዝቡንም አሰናበተና በታንኳ ወሰዱት፤ ከእነርሱም ጋር ሌሎች ታንኳዎች ነበሩ።

[37] ጽኑ ዐውሎ ነፋስም ተነሣ፤ ከሞገዱም የተነሣ ውኃው ታንኳውን እስኪሞላው ድረስ ማዕበሉ ወደ ታንኳው ይገባ ነበር።

[38] እርሱ ግን በታንኳው በስተኋላ በኩል ተንተርሶ ተኝቶ ነበር፤ ቀስቅሰውም ፥ “መምህር ሆይ፥ ስንሞት አያሳዝንህምን?” አሉት።

[39] ተነሥቶም ነፋሱን ገሠጸው፤ ባሕርዋንም ፥ “ዝም በዪ፥ ጸጥ በዪ ” አላት፤ ነፋሱም ዝም አለ፤ ፍጹም ጸጥታም ሆነ።

[40] እንዲህም አላቸው ፥ “እናንተ ደካሞች ምን ያስፈራችኋል? እንዲህስ እምነት የላችሁም?”

[41] ታላቅ ፍርሀትንም ፈሩ፤ እርስ በርሳቸውም ፥ “እንግዲህ ባሕርም፥ ነፋስም የሚታዘዙለት ይህ ማን ነው?” ተባባሉ።

የማርቆስ ወንጌል። — Chapters