[1] ዳግመኛም ወደ ምኵuራብ ገባ፤ በዚያም እጁ የሰለለች ሰው ነበር።
[2] ሊከስሱትም በሰንበት ይፈውሰው እንደ ሆነ ብለው ይጠባበቁት ነበር።
[3] ያን እጁ የሰለለችውን ሰውም “ተነሣና በመካከል ቁም ” አለው።
[4] “በሰንበት መልካም ማድረግ ይገባልን? ወይስ ክፉ ማድረግ? ነፍስ ማዳን? ወይስ መግደል?” አላቸው፤ እነርሱ ግን ዝም አሉ።
[5] ጌታችን ኢየሱስም ስለ ልቡናቸው ድንዛዜ እያዘነ ተቈጥቶ ተመለከታቸው፤ ያንም ሰው ፥ “እጅህን ዘርጋ ” አለው፤ እጁንም ዘረጋ፤ ዳነችም።
[6] ያንጊዜም ፈሪሳውያን ወጥተው ሊገድሉት ከሄሮድስ ሰዎች ጋር ተማከሩ።
[7] ጌታችን ኢየሱስም ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወደ ባሕር ሄደ፤ ከይሁዳ፥ ከገሊላም ብዙ ሰዎች ተከተሉት።
[8] እጅግ ብዙ ሰዎችም ያደረገውን ሁሉ ሰምተው ከይሁዳ፥ ከኢየሩሳሌም፥ ከኤዶምያስም፥ ከዮርዳኖስ ማዶ፥ ከጢሮስና ከሲዶናም ወደ እርሱ መጡ።
[9] ሰዎችም እንዳይጋፉት፥ ታንኳን ያቆዩለት ዘንድ ደቀ መዛሙርቱን አዘዛቸው።
[10] ብዙ ሰዎችን አድኗልና፤ ሥቃይ ያለባቸው ሁሉ እርሱን ለመዳሰስ ይጋፉበት ነበር።
[11] ርኩሳን መናፍስት የያዟቸውም ባዩት ጊዜ፥ በፊቱ ወድቀው ፥ “በእውነት አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህ ” እያሉ ጮኹ።
[12] እንዳይገልጹትም እጅግ ገሠጻቸው።
[13] ወደ ተራራም ወጣና የወደዳቸውን ጠራ፤ ወደ እርሱም መጡ።
[14] ከእርሱም ጋር እንዲኖሩና ለመስበክም ይልካቸው ዘንድ ዐሥራ ሁለቱን መርጦ ሐዋርያት አላቸው።
[15] አጋንንትን እንዲያወጡ፥ ድውያንንም እንዲፈውሱ ሥልጣንን ሰጣቸው።
[16] በየስማቸውም ጠራቸው፤ ስምዖንን “ጴጥሮስ ” ብሎ ሰየመው።
[17] የዘብዴዎስ ልጅ ያዕቆብንና የያዕቆብን ወንድም ዮሐንስንም “ቦአኔርጌስ ” ብሎ ሰየማቸው፤ “የነጐድጓድ ልጆች ” ማለት ነው።
[18] እንድርያስንና ፊልጶስን፥ በርተሎሜዎስንና ማቴዎስን፥ ቶማስንና የእልፍዮስ ልጅ ያዕቆብን፥ ታዴዎስንና ቀነናዊውን ስምዖንንም፥
[19] አሳልፎ የሰጠውን ያስቆሮቱን ይሁዳንም።
[20] ወደ ቤትም በገባ ጊዜ፥ እህል ይበላ ዘንድ እንኳ እስኪአስቸግሩት ድረስ እንደ ገና ብዙ ሰዎች ተሰበሰቡ።
[21] ዘመዶቹም ሰምተው ልቡ ዘንጋ ብሎታል ብለዋቸዋልና ሊይዙት መጡ።
[22] ከኢየሩሳሌም የወረዱ ጻፎችም ፥ “ብዔል ዜቡል ይዞታል፤ ደግሞም በአጋንንት አለቃ አጋንንትን ያወጣል ” አሉ።
[23] ጌታችን ኢየሱስም ጠርቶ በምሳሌ እንዲህ አላቸው ፥ “ሰይጣን ሰይጣንን ሊያወጣ እንዴት ይችላል?
[24] መንግሥትም እርስ በርስዋ ከተለያየች ያች መንግሥት አትጸናም።
[25] ቤትም እርስ በርሱ ከተለያየ ያ ቤት አይጸናም።
[26] ሰይጣንም አንዱ በአንዱ ላይ ቢነሣና እርስ በርሱ ቢለያይ መጨረሻ ይሆናል እንጂ አይጸናም።
[27] ኀይለኛውን አስቀድሞ ካላሰረ ወደ ኀይለኛው ቤት መግባት፥ ገንዘቡንም መበርበር የሚችል የለም፤ ከዚያ በኋላ ግን ቤቱን ይበረብራል።
[28] “እውነት እላችኋለሁ፤ ኀጢአት፥ ስድብም ሁሉ ለሰው ልጆች ይሰረይላቸዋል።
[29] በመንፈስ ቅዱስ ላይ የሚሳደብ ሁሉ ግን የዘለዓለም ፍርድ ይፈረድበታል እንጂ አይሰረይለትም።”
[30] ርኩስ መንፈስ አለበት ብለዋልና።
[31] እናቱና ወንድሞቹም መጥተው በውጭ ቆመው ሊጠሩት ወደ እርሱ ላኩ።
[32] ብዙዎችም ሰዎች አብረውት ተቀምጠው ነበሩና ፥ “እናትህና ወንድሞችህ እነሆ በውጭ ቆመዋል፤ አንተንም ይፈልጉሃል ” አሉት።
[33] እርሱም መልሶ እንዲህ አላቸው ፥ “እናቴ ማን ናት? ወንድሞቼስ እነማን ናቸው?”
[34] በዙሪያው ተቀምጠው ወደ ነበሩትም ተመልክቶ ፥ “እነሆ እናቴም ወንድሞቼም እነዚህ ናቸው
[35] የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርግ ሁሉ፥ እርሱ ወንድሜም፥ እኅቴም፥ እናቴም ነውና።”