[1] ጌታችን ኢየሱስም ይህን ነገር ተናግሮ ዐይኖቹን ወደ ሰማይ አነሣና እንዲህ አለ ፥ “አባት ሆይ፥ ሰዓቱ ደርሶአልና ልጅህ ያከብርህ ዘንድ ልጅህን አክብረው፤
[2] ሥጋ በለበሰው ሁሉ ላይ ሥልጣንን እንደ ሰጠኸው መጠን ለሰጠኸው ሁሉ የዘለዓለም ሕይወትን ይሰጣቸው ዘንድ።
[3] ብቻህን እውነተኛ አምላክ የሆንህ አንተን፥ የላክኸውንም ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ ዘንድ ይህች የዘለዓለም ሕይወት ናት።
[4] እኔ ልሠራው የሰጠኸኝን ሥራ ፈጽሜ በምድር ላይ አከበርሁህ።
[5] አሁንም አባት ሆይ፥ ዓለም ሳይፈጠር ከአንተ ጋር በነበረኝ ክብር በአንተ ዘንድ አክብረኝ።
[6] “ከዓለም ለይተህ ለሰጠኸኝ ሰዎች ስምህን ገለጥሁ፤ ያንተ ነበሩ፤ እነርሱንም ለእኔ ሰጥተኸኛል፤ ቃልህንም ጠበቁ።
[7] የሰጠኸኝም ሁሉ ከአንተ እንደ ሆነ ዛሬ ዐወቁ።
[8] የሰጠኽኝን ቃል ሰጥቻቸዋለሁና፤ እነርሱም ተቀብለው ከአንተ እንደ ወጣሁ በእውነት ዐወቁ፤ አንተም እንደ ላክኸኝ አመኑ።
[9] እኔ ስለ እነርሱ እለምናለሁ፤ የምለምንህ ስለ ዓለም አይደለም፤ ስለ ሰጠኸኝ ነው እንጂ፤ ያንተ ናቸውና።
[10] የእኔም የሆነ ሁሉ የአንተ ነው፤ የአንተም የሆነ የእኔ ነው፤ እኔም በእነርሱ ከብሬአለሁ።
[11] እንግዲህ በዓለም አልኖርም፤ እነርሱ ግን በዓለም ይኖራሉ፤ እኔም ወደ አንተ እመጣለሁ፤ ቅዱስ አባት ሆይ፥ እነዚህን የሰጠኸኝን እንደ እኛ አንድ ይሆኑ ዘንድ በስምህ ጠብቃቸው፤
[12] እኔ በዓለም ከእነርሱ ጋር ሳለሁ ግን የሰጠኸኝን በስምህ እጠብቃቸው ነበር፤ ጠበቅኋቸውም፤ የመጽሐፉም ቃል ይፈጸም ዘንድ ከጥፋት ልጅ በቀር ከእነርሱ አንድ ስንኳን አልጠፋም።
[13] አሁን ግን ወደ አንተ እመጣለሁ፤ በእነርሱም ደስታዬ ፍጹም ይሆን ዘንድ ይህን በዓለም እናገራለሁ።
[14] እኔ ቃልህን ሰጠኋቸው፤ ዓለም ግን ጠላቸው፤ እኔ ከዓለም እንዳይደለሁ እነርሱ ከዓለም አይደሉምና።
[15] ከክፉ ነገር እንድትጠብቃቸው ነው እንጂ ከዓለም እንድትለያቸው አልለምንም።
[16] እኔ ከዓለም እንዳይደለሁ ከዓለም አይደሉምና።
[17] በእውነትህ ቀድሳቸው፤ ቃልህ እውነት ነውና።
[18] አንተ እኔን ወደ ዓለም እንደ ላክኸኝ እኔም እነርሱን ወደ ዓለም ላክኋቸው።
[19] እነርሱም በእውነት ቅዱሳን ይሆኑ ዘንድ ስለ እነርሱ እኔ ራሴን እቀድሳለሁ።
[20] “የምለምንህም ስለ እነዚህ ብቻ አይደለም፤ በቃላቸው ስለሚያምኑብኝም ነው እንጂ፤
[21] ሁሉም አንድ ይሆኑ ዘንድ፥ አንተ አብ በእኔ እንዳለህ፥ እኔም በአንተ እንዳለሁ፥ እነርሱም እንደ እኛ በእኛ አንድ ይሆኑ ዘንድ፥ አንተም እንደ ላክኸኝ ዓለም ያምን ዘንድ።
[22] እኔም የሰጠኸኝን ክብር ሰጠኋቸው፤ እኛ አንድ እንደሆን እነርሱም እንደ እኛ አንድ ይሆኑ ዘንድ።
[23] እኔ በእነርሱ እኖራለሁ፤ አንተም በእኔ፤ በአንድ ፍጹማን ይሆኑ ዘንድ፤ አንተም እንደ ላክኸኝና እንደ ወደድኸኝ እኔም እነርሱን እንደ ወደድኋቸው።
[24] አባት ሆይ፥ የሰጠኸኝ እነዚህ እኔ ባለሁበት አብረውኝ ይኖሩ ዘንድና የሰጠኸኝን ክብሬን ያዩ ዘንድ እወድዳለሁ፤ ዓለም ሳይፈጠር ወድደኸኛልና።
[25] ጻድቅ አባት ሆይ፥ ዓለም አላወቀህም፤ እኔ ግን ዐወቅሁህ፤ እነዚህም አንተ እንደ ላክኸኝ ዐወቁ።
[26] እኔን የወደድህበት ፍቅር በእነርሱ ይኖር ዘንድ፥ እኔም በእነርሱ እኖር ዘንድ ስምህን ነገርኋቸው፤ ደግሞም እነግራቸዋለሁ፤”