[1] “እውነተኛ የወይን ሐረግ እኔ ነኝ፤ ተካዩም አባቴ ነው።
[2] በእኔ ያለውን፥ ፍሬ የማያፈራውን ቅርንጫፍም ሁሉ ያስወግደዋል፤ የሚያፈራውን ቅርንጫፍ ሁሉ ግን በብዙ እንዲያፈራ ያጠራዋል።
[3] እናንተ ግን ስለ ነገርኋችሁ ቃል ፈጽማችሁ ንጹሓን ናችሁ።
[4] በእኔ ኑሩ፤ እኔም በእናንተ፤ ቅርንጫፍ በወይኑ ግንድ ከአልኖረ ብቻውን ሊያፈራ እንደማይችል እናንተም እንዲሁ በእኔ ካልኖራችሁ ፍሬ ማፍራት አትችሉም።
[5] እኔ የወይን ግንድ ነኝ፤ ቅርንጫፎቹም እናንተ ናችሁ፤ በእኔ የሚኖር እኔም በእርሱ፥ ብዙ ፍሬ የሚያፈራ እርሱ ነው፤ ያለ እኔ ምንም ማድረግ አትችሉምና።
[6] በእኔ የማይኖር ቢኖር እንደ ደረቅ ቅርንጫፍ ወደ ውጭ ይጥሉታል፤ ሰብስበውም በእሳት ያቃጥሉታል።
[7] በእኔም ብትኖሩ ቃሌም በእናንተ ቢኖር የምትሹትን ሁሉ ትለምናላችሁ፤ ይደረግላችሁማል።
[8] ብዙ ፍሬ ብታፈሩ፥ ደቀ መዛሙርቴም ብትሆኑ በዚህ አባቴ ይከበራል።
[9] አብ እንደ ወደደኝ እንዲሁ ወደድኋችሁ፤ በፍቅሬም ኑሩ።
[10] የምትወዱኝ ብትሆኑ ትእዛዜን ጠብቁ፤ እኔ የአባቴን ትእዛዝ እንደ ጠበቅሁ፥ በፍቅሩም እንደምኖር እናንተም ትእዛዜን ብትጠብቁ በፍቅሬ ትኖራላችሁ።
[11] ደስታዬ በእናንተ ይኖር ዘንድ፥ ደስታችሁም ፍጹም ይሆን ዘንድ ይህን ነገርኋችሁ።
[12] “እኔ እንደ ወደድኋችሁ እርስ በርሳችሁ እንድቷደዱ የእኔ ትእዛዝ ይህች ናት።
[13] ስለ ወዳጆቹ ሕይወቱን አሳልፎ የሚሰጥ ሰው ያለ እንደ ሆነ ከዚህ የሚበልጥ ፍቅር የለም።
[14] እናንተስ ያዘዝኋችሁን ሁሉ ካደረጋችሁ ወዳጆቼ ናችሁ።
[15] እንግዲህ ወዲህ ባሮች አልላችሁም፤ ባሪያ ጌታው የሚያደርገውን አያውቅምና፤ እናንተን ግን ወዳጆቼ እላችኋለሁ፤ በአባቴ ዘንድ የሰማሁትን ሁሉ ነግሬአችኋለሁና።
[16] እኔ መረጥኋችሁ እንጂ እናንተ የመረጣችሁኝ አይደለም፤ እንድትሄዱ፥ ፍሬም እንድታፈሩ፥ ፍሬአችሁም እንዲኖር፤ አብንም በስሜ የምትለምኑት ነገር ቢኖር ሁሉን እንዲሰጣችሁ ሾምኋችሁ።
[17] እርስ በርሳችሁም እንድቷደዱ ይህን አዝዣችኋለሁ።
[18] “ዓለም ቢጠላችሁ አስቀድሞ እኔን እንደ ጠላ ዕወቁ።
[19] እናንተስ ከዓለም ብትሆኑ ዓለም በወደዳችሁ ነበር፤ ዓለም ወገኖቹን ይወዳልና፤ ነገር ግን እኔ ከዓለም መረጥኋችሁ እንጂ እናንተ ከዓለም አይደላችሁምና ስለዚህ ዓለም ይጠላችኋል።
[20] እኔ ፥ ከጌታው የሚበልጥ አገልጋይ የለም ያልኋችሁን ቃሌን ዐስቡ፤ እኔን ካሳደዱ እናንተንም ያሳድዱአችኋል፤ ቃሌን ጠብቀው ቢሆንስ ቃላችሁንም በጠበቁ ነበር።
[21] ነገር ግን ስለ ስሜ ይህን ሁሉ ያደርጉባችኋል፤ የላከኝን አያውቁትምና።
[22] ባልመጣሁና ባልነገርኋቸውስ ኖሮ ኀጢአት ባልሆነባቸውም ነበር፤ አሁን ግን ለኀጢአታቸው ምክንያት የላቸውም።
[23] እኔን የሚጠላ አባቴን ይጠላል።
[24] ሌላ ያልሠራውን ሥራ በመካከላቸው ባልሠራ ኖሮ ኀጢአት ባልሆነባቸውም ነበር፤ አሁን ግን እኔንም አባቴንም አይተዋል፤ ጠልተውማል።
[25] ነገር ግን በኦሪታቸው ፥ በከንቱ ጠሉኝ ተብሎ የተጻፈው ቃል ይፈጸም ዘንድ ነው።
[26] “እኔ ከአብ ዘንድ የምልክላችሁ ጰራቅሊጦስ እርሱም ከአብ የሚወጣ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ፥ እርሱ ስለ እኔ ይመሰክራል።
[27] እናንተም ትመሰክራላችሁ፤ ከጥንት ጀምሮ ከእኔ ጋር ኑራችኋልና።