Skip to content
Opens in a new window
Listen to this chapter • 2:52

[1] እንግዲህ እኔ ከእነርሱ ጋር ሽማግሌ፥ የክርስቶስም መከራ ምስክር፥ ደግሞም ሊገለጥ ካለው ክብር ተካፋይ የሆንሁ በመካከላቸው ያሉትን ሽማግሌዎችን እማልዳቸዋለሁ።

[2] በእናንተ ዘንድ ያሉትን የእግዚአብሔርን መንጋዎች ጠብቁ፤ ስትጠብቁአቸውም እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ በውድ እንጂ በግድ አይሁን፤ በበጎ ፈቃድ እንጂ መጥፎውን ረብ በመመኘትም አይሁን።

[3] ለመንጋዉ ምሳሌ ሁኑ እንጂ ሕዝቡን በኀይል አትግዙ።

[4] የእረኟችም አለቃ በተገለጠ ጊዜ የማይጠፋውን የክብር አክሊል ትቀበላላችሁ።

[5] እንዲሁ እናንተ ጐልማሶች ሆይ፥ ለሽማግሌዎች ተገዙ፤ ሁላችሁም ትሕትናን ልበሷት፤ እግዚአብሔር ትዕቢተኟችን ያዋርዳልና፤ ራሳቸውን ዝቅ የሚያደርጉትን ግን ያከብራቸዋል።

[6] እንግዲህ በጐበኛችሁ ጊዜ ከፍ ከፍ ያደርጋችሁ ዘንድ ከጸናችው ከእግዚአብሔር ክንድ በታች ራሳችሁን አዋርዱ።

[7] እርሱ ስለ እናንተ ያስባልና የሚያስጨንቃችሁን ሁሉ በእርሱ ላይ ጣሉት።

[8] እንግዲህ ዐዋቂዎች ሁኑ፤ ትጉም፤ ጠላታችሁ ጋኔን የሚውጠውን ፈልጎ፥ እንደሚያገሳ አንበሳ ይዞራልና።

[9] እርሱንም በእምነት ጸንታችሁ ተቃወሙት፤ እንዲህም ያለ መከራ በዓለም በአሉ ወንድሞቻችሁ ሁሉ እንደሚፈጸም ዕወቁ፤ ፍቅርንም አጽንታችሁ ያዙአት።

[10] በኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ዘለዓለም ክብሩ የጠራችሁ የጸጋ ሁሉ አምላክ ለጥቂት ጊዜ መከራን ከተቀበላችሁ በኋላ ፍጹማን ያደርጋችኋል፤ ያጸናችኋል፤ ልባሞችም ያደርጋችኋል።

[11] ለእርሱ ክብርና ኀይል እስከ ዘለዓለም ይሁን፤ አሜን።

[12] ከታመነው ወንድማችን ከስልዋኖስ ጋር እንደ ዐሰብሁ እየማለድሁ የጸናችሁባት፥ ይህቺ በእውነት የእግዚአብሔር ጸጋ እንደ ሆነች እየመሰከርሁ ጥቂት ጻፍሁላችሁ።

[13] በግብፅ በምትገኘው ባቢሎን ያለችው ከእናንተ ጋር የተመረጠችው ቤተ ክርስቲያን ሰላም ትላችኋለች፤ ልጄ ማርቆስም ሰላም ይላችኋል።

[14] ፍቅር ባለው ሰላምታ እርስ በርሳችሁ ሰላም ተባባሉ፤ በክርስቶስ አምናችሁ ያላችሁ ሁላችሁም በስምምነት ኑሩ። አሜን። መጀመሪያዪቱ የጴጥሮስ መልእክት ተፈጸመች። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን። አሜን።

የጴጥሮስ መልእክት። — Chapters