[1] እንዲሁ እናንተ ሚስቶች ሆይ፥ ከእነርሱ አንዳንዱ ለቃሉ የማይታዘዝ ቢኖር ከሴቶች መልካም ሥራ የተነሣ ያዩ ዘንድ፥ ያለ ጥርጥርም ሰውነታቸውን ይጠቅሙአት ዘንድ ለባሎቻችሁ ተገዙ።
[2] እየፈራችሁም በንጽሕና አካሄዳችሁን አሳምሩ።
[3] ለእናንተም ጠጕuርን በመሸረብና ወርቅን በማንጠልጠል፥ ወይም ዋጋው ብዙ የሆነ ልብስን በመጐናጸፍ የውጭ ሽልማት አይሁንላችሁ።
[4] ነገር ግን በእግዚአብሔር ፊት ዋጋው እጅግ የከበረ፥ የዋህና ጸጥ ያለ መንፈስ ያለው የማይጠፋና የተሰወረ የልብ ሰውነት ይሁንላችሁ።
[5] ቀድሞም እምነታቸውን በእግዚአብሔር ላይ ያደረጉ የተቀደሱ ሴቶች እንዲሁ ለባሎቻቸው በመገዛት ራሳቸውን ያስጌጡ ነበር።
[6] እንዲሁም ሣራ ለአብርሃም ትታዘዘው ነበር፤ ጌታዬም ትለው ነበር፤ እናንተም ከሚያስደነግጥ ነገር ምንም ሳትፈሩ በበጎ ሥራ ልጆችዋ ሁኑ።
[7] እንዲሁም እናንተ ባሎች ሆይ፥ ከሚስቶቻችሁ ጋር ስትኖሩ፥ ሚስቶቻችሁን አታቃልሉ፤ የሴቶች ተፈጥሮአቸው ደካማ ነውና፤ ጸሎታችሁ እንዳትሰናከል ሚስቶቻችሁን አክብሩ፥ እነርሱ ከእናንተ ጋር ክብርንና ሕይወትን ይወርሳሉና።
[8] የሁሉም ፍጻሜ የባልንጀራችሁን መከራ እየተቀበላችሁ አንድ ልብ ትሆኑ ዘንድ ነው፤ እንደ ወንድሞችም ተዋደዱ፤ ርኅሩኆችና ትሑታንም ሁኑ፤
[9] ክፉ ላደረገባችሁ ክፉ አትመልሱ፤ የሰደባችሁንም አትስደቡ፤ ጠላታችሁንም መርቁ፤ በረከትን ትወርሱ ዘንድ ለዚህ ተጠርታችኋልና።
[10] “ሕይወትን የሚወድ፥ መልካሞችንም ቀኖች ሊያይ የሚሻ፥ አንደበቱን ከክፉ፥ ከንፈሮቹንም ተንኰልን ከመናገር ይከልክል፤
[11] ከክፉ ይራቅ፤ መልካምንም ያድርግ፤ ሰላምን ይሻት፥ ይከተላትም።
[12] የእግዚአብሔር ዐይኖቹ ወደ ጻድቃኑ ናቸውና፤ ጆሮዎቹም ወደ ልመናቸው ናቸው፤ የእግዚአብሔር ፊት ክፉ ወደሚሠሩ ሰዎች ናት።”
[13] በጎንም ለማድረግ ብትቀኑ ክፉ ሊያደርግባችሁ የሚወድ ማነው?
[14] ነገር ግን ስለ ጽድቅ እንኳ መከራን ብትቀበሉ ብፁዓን ናችሁ፤ የሚያስፈራራችሁንም አትፍሩ፤ አትደንግጡም።
[15] ነገር ግን በፍጹም ልቡናችሁ እግዚአብሔርን አመስግኑት፤ በእናንተም ስላለች ተስፋ ምክንያት ለሚጠይቌችሁ ሁሉ መልስ ለመስጠት ሁልጊዜ ተዘጋጅታችሁ ኑሩ።
[16] ሥራችሁንም ክፉ አስመስለው የሚያሙአችሁ ሰዎች ቢኖሩ፥ ስለ ክርስቶስ ከምትሠሩት ከሥራችሁ ደግነት የተነሣ የሚያሙአችሁ ሰዎች ያፍሩ ዘንድ በቅንነታችሁና እግዚአብሔርን በመፍራት አካሄዳችሁን አሳምሩ።
[17] ክፉ ከምትሠሩ ይልቅ መልካም ሥራ እየሠራችሁ፥ የእግዚአብሔርንም ፈቃድ እየተከተላችሁ መከራ ብትቀበሉ ይሻላልና።
[18] ክርስቶስም ስለ ሰው ኀጢአት አንድ ጊዜ ሞቶአልና፤ ጻድቅ እርሱ እኛን ወደ እግዚአብሔር ያቀርበን ዘንድ ስለ እኛ ስለ ኀጢአታችን በሥጋ ሞተ፤ በመንፈስ ግን ሕያው ነው።
[19] በእርሱም በወኅኒ ወደ አሉ ነፍሳት ሄዶ ነጻነትን ሰበከላቸው።
[20] ጥቂቶች ማለት ስምንት ነፍሳት በውኃ የዳኑባትን መርከብ ሲሠራ በኖኅ ዘመን የእግዚአብሔር ትዕግሥት በዘገየ ጊዜ፥ ቀድሞ ክደውት ለነበሩት ሰበከላቸው።
[21] አሁንም እኛን በዚያው አምሳል በጥምቀት ያድነናል፤ ሥጋን ከዕድፍ በመታጠብ አይደለም፤ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመነሣቱ በእግዚአብሔር እንድናምን መልካም ግብርን ያስተምረን ዘንድ ነው እንጂ።
[22] እርሱም ወደ ሰማይ ያረገ፥ በእግዚአብሔርም ቀኝ ተቀምጦ ያለ፥ መላእክትና ሥልጣናት፥ ኀይላትም የተገዙለት ነው።