Skip to content
Opens in a new window
Listen to this chapter • 3:11

[1] እናንተም በኀጢአታችሁ ምውታን ሆናችሁ ነበር።

[2] ይኸውም ቀድሞ በዚህ ዓለም ሥርዐት፥ አሁን በከሓድያን ልጆች የሚበረታታባቸውና፥ በነፋስ አምሳል የሚገዛቸው አለቃ እንደ ነበረው ፈቃድ ጸንታችሁ የነበራችሁበት ነው።

[3] እኛ ሁላችን ቀድሞ እንደ ሥጋችን ምኟት ኖርን፤ የሥጋችንንም ፈቃድና ያሰብነውን አደረግን፤ እንደ ሌሎች ኃጥአንም ሁሉ የጥፋት ልጆች ሆንን።

[4] እግዚአብሔር ግን በምሕረቱ ባለጸግነትና በወደደን በፍቅሩ ብዛት፥

[5] በኃጢአታችን የሞትን ሳለን በክርስቶስ ሕይወትን ሰጠን፤ በጸጋውም ዳንን።

[6] በኢየሱስ ክርስቶስም አስነሥቶ በሰማያት ከእርሱ ጋር አኖረን።

[7] በኢየሱስ ክርስቶስ ይቅር ስላለን የጸጋውን ባለጠግነት ብዛት በሚመጣው ዓለም ይገልጥ ዘንድ፥

[8] አምነን በጸጋው ድነናልና፤ ይህም የእግዚአብሔር ጸጋ ነው እንጂ የእናንተ ሥራ አይደለም።

[9] የሚመካም እንዳይኖር በምግባራችን አይደለም።

[10] እንመላለስበት ዘንድ እግዚአብሔር አስቀድሞ ላዘጋጀው በጎ ሥራ በኢየሱስ ክርስቶስ የፈጠረን ፍጥረቱ ነንና።

[11] እናንተ አሕዛብ አስቡ፤ ቀድሞ በሥጋ ሥርዐት ነበራችሁ፤ ያልተገዘሩም ይሉአችሁ ነበር፤ እንዲህ የሚሉአችሁም የተገዘሩ ሰዎች ናቸው፤ ግዝረት ግን በሥጋ ላይ የሚደረግ የሰው እጅ ሥራ ነው።

[12] ያንጊዜ ክርስቶስን አታውቁትም ነበር፤ ከእስራኤል ሕግ የተለያችሁ ነበራችሁ፤ ከተስፋው ሥርዐትም እንግዶች ነበራችሁ፤ ተስፋም አልነበራችሁም፤ በዚህም ዓለም እግዚአብሔርን አታውቁትም ነበር።

[13] አሁን ግን ቀድሞ ርቃችሁ የነበራችሁ እናንተ በኢየሱስ ክርስቶስ ሆናችሁ በክርስቶስ ደም ቀረባችሁ።

[14] ሁለቱን አንድ ያደረገ ሰላማችን እርሱ ነውና፥ በሥጋውም በመካከል የነበረውን የጥል ግድግዳ አፍርሶ ጥልን ሻረ።

[15] ሁለቱንም አድሶ አንድ ያደርጋቸው ዘንድ በሥርዐቱ የትእዛዝን ሕግ አጠፋ፤ ዕርቅንም አደረገ።

[16] በመስቀሉም በአንድ ሥጋው ሁለቱን ወደ እግዚአብሔር አቀረባቸው፤ በእርሱም ጥልን አጠፋ።

[17] መጥቶም፤ ቀርበን ለነበርነው ሰላምን፥ ርቃችሁ ለነበራችሁት ለእናንተም ሰላምን ሰጠን።

[18] እርሱ መርቶናልና፤ ሁለታችንንም በመንፈስ ቅዱስ ወደ አባቱ አቅርቦናልና።

[19] እንግዲህስ ወዲህ እናንተ ከቅዱሳን ጋር ባላገሮችና የእግዚአብሔር ቤተ ሰቦች እንጂ እንግዶችና መጻተኟች አይደላችሁም።

[20] በነቢያትና በሐዋርያት መሠረት ላይ ታንጻችኋልና የሕንጻው የማዕዘን ራስ ድንጋይም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፤

[21] እርሱም ሕንጻ ሁሉ የሚያያዝበት፥ የእግዚአብሔርም ቤተ መቅደስ ግንብ የሚያድግበት ነው።

[22] እናንተ በመንፈስ ቅዱስ የእግዚአብሔር ማደሪያ ልትሆኑ በእርሱ ታነጻችሁ።

ወደ ኤፌሶን ሰዎች። — Chapters