[1] በአንጿኪያ በነበረችው ቤተ ክርስቲያንም ነቢያትና መምህራን ነበሩ፤ እነርሱም በርናባስ፥ ኔጌር የተባለው ስምዖን፥ የቀሬናው ሉቅዮስ፥ ከአራተኛው ክፍል ገዢ ከሄሮድስ ጋር ያደገው ምናሔ፥ ሳውልም ነበሩ።
[2] የእግዚአብሔርን ሥራ ሲሠሩ፥ ሲጿሙም መንፈስ ቅዱስ ፥ “በርናባስንና ሳውልን እኔ ለፈለግኋቸው ሥራ ለዩልኝ ” አላቸው።
[3] ያንጊዜም ከጿሙና ከጸለዩ፥ እጃቸውንም በራሳቸው ላይ ከጫኑባቸው በኋላ ላኩአቸው።
[4] ከመንፈስ ቅዱስም ተልከው ወደ ሴሌውቅያ ወረዱ፤ ከዚያም በመርከብ ወደ ቆጵሮስ ሄዱ።
[5] ወደ ሰልሚና ሀገርም ገብተው በአይሁድ ምኵuራቦች የእግዚአብሔርን ቃል አስተማሩ፤ ዮሐንስም እየአገለገላቸው ከእነርሱ ጋር ነበር።
[6] በደሴቲቱም ሁሉ ሲዘዋወሩ ጳፉ ወደምትባል ሀገር ደረሱ፤ በዚያም አንድ አይሁዳዊ የሆነ ሐሰተኛ ነቢይና አስማተኛ ሰው አገኙ፤ ስሙም በርያሱስ ይባላል።
[7] እርሱም ብልህ ሰው በሆነ ሰርግዮስ ጳውሎስ በሚባል አገረ ገዢ ዘንድ ይኖር ነበረ። የእግዚአብሔርንም ቃል ሊሰማ ወድዶ በርናባስንና ሳውልን ወደ እርሱ ጠራቸው።
[8] አስማተኛው ኤልማስም የስሙ ትርጓሜ እንዲህ ነበረና፥ ገዥውን ከማመን ሊከለክለው ፈልጎ ተቃወማቸው።
[9] ጳውሎስ በተባለው በሳውል ላይም ቅዱስ መንፈስ ሞላበት፤ አተኵuሮም ተመለከተው።
[10] እንዲህም አለው ፥ “ሽንገላንና ክፋትን ሁሉ የተመላህ፥ የሰይጣን ልጅ፥ የጽድቅ ሁሉ ጠላት ሆይ፥ የቀናውን የእግዚአብሔርን መንገድ ማጣመምህን ትተው ዘንድ እንቢ አልህን?
[11] እነሆ፥ አሁን የእግዚአብሔር እጅ በአንተ ላይ ነው፤ ዕውርም ትሆናለህ፤ እስከ ጊዜውም ፀሐይን አታይም፤” ወዲያውኑም ታወረ፤ ጨለማም ዋጠው፤ የሚመራውም ፈለገ።
[12] አገረ ገዢውም የሆነውን በአየ ጊዜ ተገረመ፤ በጌታችን ትምህርትም አመነ።
[13] ከዚህም በኋላ እነ ጳውሎስ ከጳፉ ከተማ ወጥተው ሄዱና የጵንፍልያ አውራጃ ወደምትሆን ወደ ጰርጌን ገቡ፤ ዮሐንስ ግን ትቶአቸው ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሰ።
[14] እነርሱም ከጰርጌን አልፈው የጲስድያ አውራጃ ወደምትሆን ወደ አንጿኪያ ደረሱ፤ በሰንበት ቀንም ወደ ምኵuራብ ገብተው ተቀመጡ።
[15] ኦሪትንና ነቢያትን ካነበቡ በኋላም የምኵuራቡ አለቆች ፥ “እናንተ ወንድሞቻችን ሆይ፥ ለሕዝብ ሊነገር የሚገባው የምክር ቃል እንደ አላችሁ ተናገሩ ” ብለው ላኩባቸው።
[16] ጳውሎስም ተነሥቶ ዝም እንዲሉ አዘዘና እንዲህ አላቸው ፥ “እናንት የእስራኤል ሰዎችና እግዚአብሔርንም የምትፈሩ ሁሉ፥ ስሙ።
[17] የእስራኤል ሕዝብ አምላክ አባቶቻችንን መረጣቸው፤ ወገኖቹንም በተሰደዱበት በምድረ ግብፅ ከፍ ከፍ አደረጋቸው፤ ከዚያም ከፍ ባለ ክንዱ አወጣቸው።
[18] አርባ ዘመንም በምድረ በዳ መገባቸው።
[19] ሰባቱን የከነዓንን አሕዛብ አጥፍቶ ምድራቸውን አወረሳቸው።
[20] ከዚህም በኋላ አራት መቶ አምሳ ዓመት እስከ ነቢዩ እስከ ሳሙኤል ዘመን ድረስ መሳፍንትን ሾመላቸው።
[21] ከዚያም ወዲያ ንጉሥ ያነግሥላቸው ዘንድ ለመኑ፤ እግዚአብሔርም ከብንያም ነገድ የተወለደውን ሰው የቂስን ልጅ ሳኦልን አርባ ዓመት አነገሠላቸው።
[22] እርሱንም ሻረው፤ ከእርሱም በኋላ ዳዊትን አነገሠላቸው፤ ‘የእሴይን ልጅ ዳዊትን ፈቃዴን ሁሉ የሚፈጽም እንደ ልቤም የታመነ ሰው ሆኖ አገኘሁት ’ ብሎ መሰከረለት።
[23] እግዚአብሔር ተስፋ እንደ ሰጣቸው ከዳዊት ዘር ለእስራኤል መድኀኒት አድርጎ ኢየሱስን አመጣላቸው።
[24] እርሱ ከመምጣቱ አስቀድሞ ዮሐንስ ለእስራኤል ሕዝብ ሁሉ የንስሓ ጥምቀትን ሰበከላቸው።
[25] ዮሐንስም መልእክቱን ሲፈጽም እንዲህ አላቸው ፥ ‘እኔን ለምን ትጠራጠሩኛላችሁ? እርሱን አይደለሁም፤ የጫማውን ማዘቢያ ከእግሩ ልፈታ የማይገባኝ ከእኔ በኋላ እነሆ፥ ይመጣል።’
[26] “እናንተ ከአብርሃም ወገን የተወለዳችሁ ወንድሞቻችን እግዚአብሔርንም የምትፈሩ፥ ይህ የሕይወት ቃል ለእናንተ ተልኮአል።
[27] በኢየሩሳሌም የሚኖሩና አለቆቻቸው ግን እርሱን አላወቁም፤ የነቢያት መጻሕፍትንም በየሰንበቱ ሁሉ ሲያነቡ አላስተዋሉትም፤ ነገር ግን ይሙት በቃ ፈረዱበት፥ ስለ እርሱ የተጻፈውንም ሁሉ ፈጸሙበት።
[28] ለሞትም የሚያበቃ ምንም በደል ባላገኙበት ጊዜ እንዲገድለው ጲላጦስን ለመኑት።
[29] ስለ እርሱም የተጻፈውን ሁሉ ከፈጸሙ በኋላ ከመስቀል አውርደው በመቃብር ቀበሩት።
[30] እግዚአብሔር ግን ከሙታን ለይቶ አስነሣው።
[31] ከተነሣም በኋላ ከገሊላ ወደ ኢየሩሳሌም አብረውት ለወጡት ብዙ ቀን ተገለጠላቸው። እነርሱም በሕዝብ ዘንድ ምስክሮች ሆኑት።
[32] “እኛም እግዚአብሔር ለአባቶቻችን ያናገረላቸውን ተስፋ እንነግራችኋለን።
[33] በሁለተኛው መዝሙር ፥ ‘አንተ ልጄ ነህ፤ እኔ ዛሬ ወለድሁህ ’ እንዳለ ኢየሱስን አስነሥቶ ተስፋውን ለእኛ ለልጆቻቸው ፈጽሞአል።
[34] መፍረስ መበስበስንም እንዳያይ እግዚአብሔር ከሙታን ለይቶ እንዳስነሣው እንዲህ አለ ፥ ‘የታመነውን የዳዊትን ቅዱስ ተስፋ እሰጣችኋለሁ።
[35] በሌላ ስፍራም እንዲህ ይላል ፥ ‘ጻድቅህን መፍረስ መበስበስን ያይ ዘንድ አትሰጠውም።’
[36] ዳዊት ግን በዘመኑ ለእግዚአብሔር ትእዛዝ አገልግሎአል፤ እንደ አባቶቹ ሞተ፥ ተቀበረም፤ መፍረስ መበስበስንም አይቶአል።
[37] ይህ እግዚአብሔር ያስነሣው ግን መፍረስ መበስበስን አላየም።
[38] እንግዲህ ወንድሞቻችን፥ በእርሱ ኀጢአታችሁ እንደሚሰረይላችሁ ተስፋ የሰጣችሁን ዕወቁ።
[39] ከሁሉም ይልቅ በሙሴ ሕግ መጽደቅ የተሳናችሁ ናችሁ። በእርሱ ግን ያመነ ሁሉ ይጸድቃል።
[40] እንግዲህ እንዲህ የሚለው የነቢያት ቃል እንዳይደርስባችሁ ተጠንቀቁ።
[41] ‘እነሆ፥ እናንተ የምታቃልሉ፥ እዩ፤ ተደነቁም፤ ያለዚያ ግን ትጠፋላችሁ፤ ማንም ቢነግራችሁ የማታምኑትን ሥራ እኔ በዘመናችሁ እሠራለሁና።’ ”
[42] ከምኵuራብም ከወጡ በኋላ ይህን ነገር በሁለተኛው ሰንበት እንዲነግሩአቸው ማለዱአቸው።
[43] ጉባኤውም በተፈታ ጊዜ ከአይሁድና ወደ ይሁዲነት ከተመለሱት ከደጋጉ ሰዎች ብዙዎች ጳውሎስንና በርናባስን ተከተሉአቸው፤ እነርሱም በእግዚአብሔር ጸጋ ይድኑ ዘንድ እያስረዱ ነገሯቸው።
[44] በሁለተኛው ሰንበትም የከተማው ሰዎች ሁሉ የእግዚአብሔርን ቃል ይሰሙ ዘንድ ተሰበሰቡ።
[45] አይሁድም የተሰበሰበውን ብዙ ሕዝብ ባዩ ጊዜ ቀኑባቸው፤ እየተሳደቡም ጳውሎስ የተናገረውን ቃል ተቃወሙ።
[46] ጳውሎስና በርናባስም ደፍረው እንዲህ ብለው ተናገሩአቸው ፥ “የእግዚአብሔርን ቃል ለእናንተ አስቀድሞ ልንነግራችሁ ይገባል፤ እንቢ ብትሉና ራሳችሁን ለዘለዓለም ሕይወት የተዘጋጀ ባታደርጉ ግን እነሆ፥ ወደ አሕዛብ እንመለሳለን።
[47] እግዚአብሔር ፥ እስከ ምድር ዳርቻ ላሉት ሁሉ መድኀኒት ትሆን ዘንድ ለአሕዛብ ብርሃን አድርጌሃለሁ ” ብሎ አዝዞናልና።
[48] አሕዛብም ይህን ሰምተው ደስ አላቸው፤ የእግዚአብሔርንም ቃል አከበሩ፤ ለዘለዓለም ሕይወትም የተዘጋጁ ሁሉ አመኑ።
[49] የእግዚአብሔርም ቃል በሀገሩ ሁሉ ተዳረሰ።
[50] አይሁድ ግን እግዚአብሔርን የሚፈሩ የከበሩ ሴቶችንና የከተማውን ሽማግሌዎች አነሳሡአቸው፤ በጳውሎስና በበርናባስ ላይም ስደትን አስነሡ፤ ከሀገራቸውም አባረሩአቸው።
[51] እነርሱ ግን የእግራቸውን ትቢያ አራግፈውባቸው ወደ ኢቆንዮን ሄዱ።
[52] መንፈስ ቅዱስም በደቀ መዛሙርት ላይ ሞላ፤ ደስም አላቸው።