Skip to content
Opens in a new window
Listen to this chapter • 2:34

[1] ወንድሞቻችን ሆይ፥ ስለ ጌታችን ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ መምጣትና ወደ እርሱ ስለ መሰብሰባችን እንነግራችኋለን።

[2] “በመንፈስ ወይም በቃል፥ ወይም ከእኛ እንደሚመጣ፥ በመልእክት የጌታ ቀን ደርሶአል ” ብላችሁ ከአእምሮ ፈጥናችሁ እንዳትናወጡ፥ እንዳትደነግጡም ዕወቁ።

[3] በምንም የሚያስታችሁ አይኑር፤ ክህደት ሳይመጣና የዐመፅ ሰው እርሱም የጥፋት ልጅ ሳይገለጥ ያቺ ቀን አትመጣምና።

[4] ራሱን ከፍ ከፍ የሚያደርግ ፥ ለሁሉም እኔ እግዚአብሔር አምላክ ነኝ የሚል፥ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ የሚቀመጥ፥ ራሱንም እንደ እግዚአብሔር የሚያደርግ ተቃዋሚ ነው።

[5] በእናንተ ዘንድ በነበርሁ ጊዜ፥ አስቀድሜ ይህን እንደ ነገርኋችሁ አታስቡምን?

[6] ጊዜው እስኪደርስ ድረስ ከመታየት የሚከለክለውን አሁን ታውቃላችሁ።

[7] የኀጢአት ምሥጢር በእርሱ ፈጽሞ ይሠራልና፤ ዛሬ ግን ከመካከል እስኪወገድ ድረስ ተይዞአል።

[8] ያንጊዜም የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ መንፈሱ ያጠፋው ዘንድ ያለው፥ ሲመጣም በመገለጡ የሚሽረው ኀጢአተኛው የዐመፅ ልጅ ይገለጣል።

[9] የዚያ ሰው አመጣጡ በሰይጣን ሥራ፥ በኀይል ሁሉና በምልክት፥ የሐሰት ድንቅ ሥራዎችንም በመሥራት ነው።

[10] ይድኑ ዘንድ የእውነትን ፍቅር ስላልተቀበሉ ለሚጠፉትም በዐመፅ ማታለል ነው።

[11] ስለዚህም እግዚአብሔር በሐሰት ያምኑ ዘንድ የሚያስት ኀይልን ይልክባቸዋል።

[12] በእውነት የማያምኑና በዐመፅ የሚተባበሩ ሁሉ ይፈረድባቸው ዘንድ።

[13] በእግዚአብሔር የተመሰገናችሁ ወንድሞቻችን ሆይ፥ ስለ እናንተ ዘወትር እግዚአብሔርን ልናመሰግነው ይገባል፤ እግዚአብሔር በመንፈስ መቀደስ፥ እውነትንም በማመን ለመዳን በኵuር አድርጎ መርጦአችኋልና።

[14] ለዚህም የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ክብር ለማግኘት በወንጌል ትምህርት ጠራችሁ።

[15] አሁንም ወንድሞቻችን ሆይ፥ ጸንታችሁ ቁሙ፤ በቃላችንም ቢሆን፥ ወይም በመልእክታችን ያስተማርናችሁንና የሠራንላችሁን ሥርዐት ያዙ።

[16] ራሱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የወደደን፥ የዘለዓለምን መጽናናትና መልካም ተስፋንም የሰጠን እግዚአብሔር አባታችን፥

[17] እርሱ በጸጋው ልባችሁን ያጽና፤ በበጎ ምግባርና በቃልም ሁሉ ያጽናችሁ።

ወደ ተሰሎንቄ ሰዎች 2 — Chapters