[1] ወንድሞቼ ሆይ፥ በእርስዋ ቅን ልቡናችሁን ለማነቃቃት በማሰብ የጻፍሁላችሁ ሁለተኛዪቱ መልእክት ይህች ናት።
[2] የቀደሙ ቅዱሳን ነቢያት የተናገሩትን ቃልና ለእኛ ለሐዋርያትም ያዘዘውን የመድኀኒታችንና የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ትእዛዝ ታስቡ ዘንድ፥
[3] በኋለኛው ዘመን እንደ ራሳቸው ምኟት የሚመላለሱ ዘባቾች በመዘበት እንደሚመጡ ይህን በፊት ዕወቁ።
[4] እነርሱም ፥ “የመምጣቱ የተስፋ ቃል ወዴት ነው? እነሆ የቀደሙ አባቶቻችን ሞቱ፤ ፍጥረት ሁሉ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ እንደ አለ ይኖራል ” ይላሉ።
[5] ሰማያት ጥንት እንደ ተፈጠሩ፥ ምድርም ከውኃ ላይ እንደ አለች፥ በእግዚአብሔር ቃልም በውኃ ላይ እንደ ጸናች ይህን በፈቃዳቸው አያውቁትም፤
[6] ያንጊዜም የነበረው ዓለም በጥፋት ውኃ ሰጥሞ ጠፋ።
[7] አሁንም ሰማይና ምድር በዚያ ቃል ለእሳት ተዘጋጅተዋል፤ ኃጥኣን ሰዎች እስከሚጠፉበት እስከ ፍርድ ቀንም ተጠብቀዋል።
[8] ነገር ግን ወንድሞቻችን ሆይ፥ ይህን አትርሱ፤ በእግዚአብሔር ዘንድ አንዲት ቀን እንደ አንድ ሺህ ዓመት፥ ሺህ ዓመትም እንደ አንድ ቀን ነውና።
[9] እግዚአብሔር የተናገረውን ቃል አያስቀርም፤ ይቀራል ብለው የሚናገሩ አሉና፤ ነገር ግን ስለ እነርሱ ይታገሣል፤ ማንንም ያጠፋ ዘንድ አይሻምና ንስሓ ይገቡ ዘንድ ለሰው ሁሉ ዕድሜን ይሰጣል እንጂ።
[10] ሰማያት የሚነዋወጡባትና የሚያልፉባት፥ ቀድሞ የነበረው ፍጥረት ሁሉ በእሳት ነበልባል የሚቀልጥባት፥ ምድርና በእርስዋ ላይ ያለው ፍጥረት ሁሉ የሚቃጠልባት የእግዚአብሔር ቀን ግን እንደ ሌባ ድንገት ትመጣለች።
[11] ይህ ሁሉ እንዲህ የሚቀልጥ ከሆነ በተቀደሰች አካሄድና በመልካም አምልኮ ለመኖር ፍጠኑ።
[12] እግዚአብሔር የሚመጣባትን፥ ሰማያትም ቀልጠው የሚጠፉባትን፥ ፍጥረትም ሁሉ ተቃጥሎ የሚጠፋባትን ዕለት በተስፋ እየጠበቃችሁ ፍጠኑ።
[13] እኛ ግን ጽድቅ የሚኖርባቸውን አዲሶቹን ሰማያትና አዲሲቱን ምድር ተስፋ እናደርጋለን።
[14] አሁንም ወንድሞቼ ሆይ፥ ይህን ተስፋ እያደረጋችሁ ርኵuሰትና በደል የሌለባችሁ ሆናችሁና ተስማምታችሁ እንዲያገኛችሁ ፍጠኑ።
[15] የምንወደው ወንድማችን ጳውሎስ ደግሞ እግዚአብሔር በሰጠው ጥበብ እንደ ጻፈላችሁ የጌታችንን ትዕግሥት እንደ መድኀኒት ቅWጠሩት።
[16] የዚህን ነገር በተናገረባቸው መልእክታቱ ሁሉ ስለዚህ እንደ ተናገረ፥ በእነዚያ ዘንድ ለማስተዋል የሚያስቸግር ነገር አለ፤ ያልተማሩትና የማይጸኑትም ሰዎች ሌሎችን መጻሕፍት እንደሚያጣምሙ እነዚህን ደግሞ ለገዛ ጥፋታቸው ያጣምማሉ።
[17] ወንድሞቻችን ሆይ፥ እናንተስ አስቀድማችሁ ይህን ዕወቁ፤ በማይጠቅም ትምህርትም እንዳትስቱና ከጸናችሁበት እንዳትወድቁ ተጠንቀቁ።
[18] በጌታችንና በመድኀኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ዕውቀት እደጉ፤ ለእርሱ አሁንም እስከ ዘለዓለም ቀን ድረስ ክብር ይሁን፤ አሜን። ሁለተኛዪቱ የሐዋርያው የቅዱስ ጴጥሮስ መልእክት ተፈጸመች። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን። አሜን።