Skip to content
Opens in a new window

[1] አየሁም፥ እነሆም፥ በጉ በጽዮን ተራራ ቆሞ ነበር፥ ከእርሱም ጋር ስሙና የአባቱ ስም በግምባራቸው የተጻፈላቸው መቶ አርባ አራት ሺህ ነበሩ።

[2] እንደ ብዙ ውኃም ድምፅና እንደ ታላቅ ነጐድጓድ ድምፅ ያለ ከሰማይ ድምፅን ሰማሁ፥ ደርዳሪዎችም በገና እንደሚደረድሩ ያለ ድምፅ ሰማሁ።

[3] በዙፋኑም ፊት በአራቱም እንስሶችና በሽማግሌዎቹ ፊት አዲስ ቅኔ ዘመሩ፤ ከምድርም ከተዋጁት ከመቶ አርባ አራት ሺህ በቀር ያን ቅኔ ሊማር ለማንም አልተቻለውም።

[4] ከሴቶች ጋር ያልረከሱ እነዚህ ናቸው፥ ድንግሎች ናቸውና። በጉ ወደሚሄድበት የሚከተሉት እነዚህ ናቸው። ለእግዚአብሔርና ለበጉ በኵራት እንዲሆኑ ከሰዎች የተዋጁ እነዚህ ናቸው።

[5] በአፋቸውም ውሸት አልተገኘም፤ ነውር የለባቸውም።

[6] በምድርም ለሚኖሩ ለሕዝብም ለነገድም ለቋንቋም ለወገንም ሁሉ ይሰብክ ዘንድ የዘላለም ወንጌል ያለው ሌላ መልአክ ከሰማይ መካከል ሲበር አየሁ፤

[7] በታላቅ ድምፅም። የፍርዱ ሰዓት ደርሶአልና እግዚአብሔርን ፍሩ ክብርንም ስጡት፤ ሰማይንና ምድርንም ባሕርንም የውኃንም ምንጮች ለሠራው ስገዱለት አለ።

[8] ሌላም ሁለተኛ መልአክ። አሕዛብን ሁሉ የዝሙትዋን ቍጣ ወይን ጠጅ ያጠጣች ታላቂቱ ባቢሎን ወደቀች፥ ወደቀች እያለ ተከተለው።

[9] ሦስተኛም መልአክ ተከተላቸው፥ በታላቅ ድምፅ እንዲህ እያለ። ለአውሬውና ለምስሉ የሚሰግድ በግምባሩም ወይም በእጁ ምልክቱን የሚቀበል ማንም ቢኖር፥

[10] እርሱ ደግሞ በቍጣው ጽዋ ሳይቀላቅል ከተዘጋጀው ከእግዚአብሔር ቍጣ ወይን ጠጅ ይጠጣል፥ በቅዱሳንም መላእክትና በበጉ ፊት በእሳትና በዲን ይሳቀያል።

[11] የሥቃያቸውም ጢስ ለዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ ይወጣል፥ ለአውሬውና ለምስሉም የሚሰግዱ የስሙንም ምልክት የሚቀበል ሁሉ ቀንና ሌሊት ዕረፍት የላቸውም።

[12] የእግዚአብሔርን ትእዛዛት የሚጠብቁት ኢየሱስንም በማመን የሚጸኑት ቅዱሳን ትዕግሥታቸው በዚህ ነው።

[13] ከሰማይም። ከእንግዲህ ወዲህ በጌታ የሚሞቱ ሙታን ብፁዓን ናቸው። መንፈስ። አዎን፥ ከድካማቸው ያርፉ ዘንድ፥ ሥራቸውም ይከተላቸዋል ይላል ብለህ ጻፍ የሚል ድምፅ ሰማሁ።

[14] አየሁም፥ እነሆም ነጭ ደመና፥ በደመናውም ላይ የሰውን ልጅ የሚመስል ተቀምጦአል፥ በራሱም ላይ የወርቅ አክሊል በእጁም ስለታም ማጭድ ነበረው።

[15] ሌላ መልአክም ከመቅደሱ ወጥቶ በደመናው ላይ ለተቀመጠው። የማጨድ ሰዓት ስለ ደረሰ ማጭድህን ስደድና እጨድ፥ የምድሪቱ መከር ጠውልጓልና ብሎ በታላቅ ድምፅ ጮኸ።

[16] በደመናውም ላይ የተቀመጠው ማጭዱን ወደ ምድር ጣለው ምድርም ታጨደች።

[17] ሌላ መልአክም በሰማይ ካለው መቅደስ ወጣ፥ እርሱም ደግሞ ስለታም ማጭድ ነበረው።

[18] በእሳትም ላይ ሥልጣን ያለው ሌላ መልአክ ከመሠዊያው ወጥቶ ስለታም ማጭድ ያለውን። ዘለላዎቹ ፈጽመው በስለዋልና ስለታሙን ማጭድህን ስደድና በምድር ያለውን የወይን ዛፍ ዘለላዎች ቍረጥ ብሎ በታላቅ ድምፅ ጠራ።

[19] መልአኩም ማጭዱን ወደ ምድር ጣለው፥ በምድርም ካለው ከወይን ዛፍ ቈርጦ ወደ ታላቁ ወደ እግዚአብሔር ቍጣ መጥመቂያ ጣለ።

[20] የወይኑም መጥመቂያ ከከተማ ውጭ ተረገጠ፥ እስከ ፈረሶች ልጓምም የሚደርስ ደም ርቀቱ ሺህ ስድስት መቶ ምዕራፍ ሆኖ ከመጥመቂያው ወጣ።

የዮሐንስ ራእይ። የዮሐንስ ራእይ — Chapters