[1] አሁንም እናንተ ባለ ጠጎች፥ ስለሚደርስባችሁ ጭንቅ ዋይ ዋይ እያላችሁ አልቅሱ።
[2] ሀብታችሁ ተበላሽቶአል፥ ልብሳችሁም በብል ተበልቶአል።
[3] ወርቃችሁም ብራችሁም ዝጎአል፥ ዝገቱም ምስክር ይሆንባችኋል ሥጋችሁንም እንደ እሳት ይበላል። ለኋለኛው ቀን መዝገብን አከማችታችኋል።
[4] እነሆ፥ እርሻችሁን ያጨዱት የሠራተኞች ደመወዝ በእናንተ ተቀምቶ ይጮኻል፥ የአጫጆችም ድምፅ ወደ ጌታ ፀባዖት ጆሮ ገብቶአል።
[5] በምድር ላይ ተቀማጥላችኋል በሴሰኝነትም ኖራችኋል፤ ለእርድ ቀን እንደሚያወፍር ልባችሁን አወፍራችኋል።
[6] ጻድቁን ኰንናችሁታል ገድላችሁትማል፤ እናንተን አይቃወምም።
[7] እንግዲህ፥ ወንድሞች ሆይ፥ ጌታ እስኪመጣ ድረስ ታገሡ። እነሆ፥ ገበሬው የፊተኛውንና የኋለኛውን ዝናብ እስኪቀበል ድረስ እርሱን እየታገሠ የከበረውን የመሬት ፍሬ ይጠብቃል።
[8] እናንተ ደግሞ ታገሡ፥ ልባችሁንም አጽኑ፤ የጌታ መምጣት ቀርቦአልና።
[9] ወንድሞች ሆይ፥ እንዳይፈረድባችሁ እርስ በርሳችሁ አታጉረምርሙ፤ እነሆ፥ ፈራጅ በደጅ ፊት ቆሞአል።
[10] ወንድሞች ሆይ፥ የመከራና የትዕግሥት ምሳሌ የሆኑትን በጌታ ስም የተናገሩትን ነቢያትን ተመልከቱ።
[11] እነሆ፥ በትዕግሥት የጸኑትን ብፁዓን እንላቸዋለን፤ ኢዮብ እንደ ታገሠ ሰምታችኋል፥ ጌታም እንደ ፈጸመለት አይታችኋል፤ ጌታ እጅግ የሚምር የሚራራም ነውና።
[12] ከሁሉም በፊት፥ ወንድሞቼ ሆይ፥ በሰማይ ቢሆን በምድርም ቢሆን በሌላ መሐላም ቢሆን በምንም አትማሉ፤ ነገር ግን ከፍርድ በታች እንዳትወድቁ ነገራችሁ አዎን ቢሆን አዎን ይሁን፥ አይደለምም ቢሆን አይደለም ይሁን።
[13] ከእናንተ መከራን የሚቀበል ማንም ቢኖር እርሱ ይጸልይ፤ ደስ የሚለውም ማንም ቢኖር እርሱ ይዘምር።
[14] ከእናንተ የታመመ ማንም ቢኖር የቤተ ክርስቲያንን ሽምግሌዎች ወደ እርሱ ይጥራ፤ በጌታም ስም እርሱን ዘይት ቀብተው ይጸልዩለት።
[15] የእምነትም ጸሎት ድውዩን ያድናል ጌታም ያስነሣዋል፤ ኃጢአትንም ሠርቶ እንደ ሆነ ይሰረይለታል።
[16] እርስ በርሳችሁ በኃጢአታችሁ ተናዘዙ። ትፈወሱም ዘንድ እያንዳንዱ ስለ ሌላው ይጸልይ፤ የጻድቅ ሰው ጸሎት በሥራዋ እጅግ ኃይል ታደርጋለች።
[17] ኤልያስ እንደ እኛ የሆነ ሰው ነበረ፥ ዝናብም እንዳይዘንብ አጥብቆ ጸለየ፥ በምድርም ላይ ሦስት ዓመት ከስድስት ወር አልዘነበም፤ ሁለተኛም ጸለየ፥
[18] ሰማዩም ዝናብን ሰጠ ምድሪቱም ፍሬዋን አበቀለች።
[19] ወንድሞቼ ሆይ፥ ከእናንተ ማንም ከእውነት ቢስት አንዱም ቢመልሰው፥
[20] ኃጢአተኛን ከተሳሳተበት መንገድ የሚመልሰው ነፍሱን ከሞት እንዲያድን፥ የኃጢአትንም ብዛት እንዲሸፍን ይወቅ።