Skip to content
Opens in a new window

[1] ወንድሞች ሆይ፥ ለመቄዶንያ አብያተ ክርስቲያናት የተሰጠውን የእግዚአብሔርን ጸጋ እናስታውቃችኋለን፤

[2] በብዙ መከራ ተፈትነው ሳሉ የደስታቸው ብዛትና የድህነታቸው ጥልቅነት የልግስናቸውን ባለ ጠግነት አብዝቶአል፤

[3] እንደ ዓቅማቸው መጠን ከዓቅማቸውም የሚያልፍ እንኳ ወደው እንደ ሰጡ እመሰክርላቸዋለሁና።

[4] ለቅዱሳን በሆነው አገልግሎት እንዲተባበሩ ይህን ቸርነት በብዙ ልመና ከእኛ ይለምኑ ነበር፥

[5] አስቀድመውም በእግዚአብሔር ፈቃድ ራሳቸውን ለጌታ ለእኛም ሰጡ እንጂ እንዳሰብን አይደለም።

[6] ስለዚህም ቲቶ አስቀድሞ እንደ ጀመረ እንዲሁ ደግሞ ይህን ቸር ሥራ ደግሞ በእናንተ ዘንድ ሊፈጽም ለመንን።

[7] ነገር ግን በነገር ሁሉ፥ በእምነትና በቃል በእውቀትም በትጋትም ሁሉ ለእኛም በፍቅራችሁ እንደ ተረፋችሁ፥ በዚህ ቸር ሥራ ደግሞ ትረፉ።

[8] ትእዛዝ እንደምሰጥ አልልም፥ ነገር ግን በሌሎች ትጋት በኩል የፍቅራችሁን እውነተኛነት ደግሞ ልመረምር እላለሁ፤

[9] የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ቸር ስጦታ አውቃችኋልና፤ ሀብታም ሲሆን፥ እናንተ በእርሱ ድህነት ባለ ጠጎች ትሆኑ ዘንድ ስለ እናንተ ድሀ ሆነ።

[10] በዚህም ነገር ምክር እሰጣለሁ፤ ከአምና ጀምራችሁ ለማድረግ ብቻ ያይደለ ነገር ግን ለማሰብ ደግሞ አስቀድማችሁ የጀመራችሁት ይህ ይጠቅማችኋልና፤

[11] አሁንም ለማሰብ በጎ ፈቃድ እንደ ነበረ፥ እንዲሁ እንዳላችሁ መጠን መፈጸም ደግሞ ይሆን ዘንድ፥ ማድረጉን ደግሞ ፈጽሙ።

[12] በጎ ፈቃድ ቢኖር፥ እንዳለው መጠን የተወደደ ይሆናል እንጂ እንደሌለው መጠን አይደለም።

[13] ለሌሎች ዕረፍት ለእናንተም መከራ እንዲሆን አይደለም፥ ትክክል እንዲሆን ነው እንጂ፤

[14] የእነርሱ ትርፍ ደግሞ የእናንተን ጉድለት እንዲሞላ በአሁኑ ጊዜ የእናንተ ትርፍ የእነርሱን ጉድለት ይሙላ፤ በትክክል እንዲሆን፥ እንዲህ ተብሎ እንደ ተጻፈ።

[15] ብዙ ያከማቸ አላተረፈም፥ ጥቂትም ያከማቸ አላጎደለም።

[16] ነገር ግን በቲቶ ልብ ስለ እናንተ ያንን ትጋት የሰጠ አምላክ ይመስገን፤

[17] ምክራችንን ተቀብሎአልና፥ ትጋት ግን ስለ በዛበት ወዶ ወደ እናንተ ይወጣል።

[18] ከእርሱም ጋር ስለ ወንጌል ስብከት በአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ የተመሰገነውን ወንድም እንልካለን፤

[19] ይህም ብቻ አይደለም ነገር ግን የጌታን የራሱን ክብርና የእኛን በጎ ፈቃድ ለማሳየት በምናገለግለው በዚህ ቸር ሥራ ከእኛ ጋር እንዲጓደድ በአብያተ ክርስቲያናት ደግሞ ተመረጠ።

[20] ስለምናገለግለው ስለዚህ ለጋስ ስጦታ ማንም እንዳይነቅፈን እንጠነቀቃለን፤

[21] በጌታ ፊት ብቻ ያይደለ ነገር ግን በሰው ፊት ደግሞ መልካም የሆነውን እናስባለንና።

[22] ብዙ ጊዜም በብዙ ነገር መርምረን ትጉ እንደ ሆነ ያገኘነውን፥ አሁንም በእናንተ እጅግ ስለሚታመን ከፊት ይልቅ እጅግ ትጉ የሚሆነውን ወንድማችንን ከእነርሱ ጋር እንልካለን።

[23] ስለ ቲቶ የሚጠይቅ ቢኖር ስለ እናንተ አብሮኝ የሚሠራ ባልንጀራዬ ነው፤ ስለ ወንድሞቻችን የሚጠይቅ ቢኖርም የአብያተ ክርስቲያናት መልእክተኞችና የክርስቶስ ክብር ናቸው።

[24] እንግዲህ የፍቅራችሁንና ስለ እናንተ ያለውን የትምክህታችንን መግለጫ በአብያተ ክርስቲያናት ፊት ለእነርሱ ግለጡ።

ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 2 — Chapters