[1] -
[2] መንፈስ ግን በግልጥ። በኋለኞች ዘመናት አንዳንዶች የሚያስቱ መናፍስትንና በውሸተኞች ግብዝነት የተሰጠውን የአጋንንትን ትምህርት እያደመጡ፥ ሃይማኖትን ይክዳሉ ይላል፤ በገዛ ሕሊናቸው እንደሚቃጠሉ ደንዝዘው፥
[3] እነዚህ ውሸተኞች መጋባትን ይከለክላሉ፥ አምነውም እውነትን የሚያውቁ ከምስጋና ጋር ይቀበሉ ዘንድ እግዚአብሔር ከፈጠረው መብል እንዲርቁ ያዝዛሉ።
[4] እግዚአብሔር የፈጠረው ሁሉ መልካም ነውና፥ ከምስጋናም ጋር ቢቀበሉት የሚጣል ምንም የለም፤
[5] በእግዚአብሔር ቃልና በጸሎት የተቀደሰ ነውና።
[6] ስለዚህ ወንድሞችን ብታሳስብ፥ በእምነትና በተከተልኸው በመልካም ትምህርት ቃል የምትመገብ የኢየሱስ ክርስቶስ መልካም አገልጋይ ትሆናለህ።
[7] ነገር ግን ለዚህ ዓለም ከሚመችና የአሮጊቶችን ሴቶች ጨዋታ ከሚመስለው ተረት ራቅ። እግዚአብሔርን ለመምሰል ግን ራስህን አስለምድ።
[8] ሰውነትን ለሥጋዊ ነገር ማስለመድ ለጥቂት ይጠቅማልና፤ እግዚአብሔርን መምሰል ግን የአሁንና የሚመጣው ሕይወት ተስፋ ስላለው፥ ለነገር ሁሉ ይጠቅማል።
[9] ይህ ቃል የታመነ ሁሉም እንዲቀበሉት የተገባ ነው፤
[10] ይህን ለማግኘት እንደክማለንና፥ ስለዚህም እንሰደባለን፤ ይህም ሰውን ሁሉ ይልቁንም የሚያምኑትን በሚያድን በሕያው አምላክ ተስፋ ስለምናደርግ ነው።
[11] -
[12] ይህን እዘዝና አስተምር። በቃልና በኑሮ በፍቅርም በእምነትም በንጽሕናም ለሚያምኑቱ ምሳሌ ሁን እንጂ፥ ማንም ታናሽነትህን አይናቀው።
[13] እስክመጣ ድረስ ለማንበብና ለመምከር ለማስተማርም ተጠንቀቅ።
[14] በትንቢት ከሽማግሌዎች እጅ መጫን ጋር የተሰጠህን፥ በአንተ ያለውን የጸጋ ስጦታ ቸል አትበል።
[15] ማደግህ በነገር ሁሉ እንዲገለጥ ይህን አስብ፥ ይህንም አዘውትር።
[16] ለራስህና ለትምህርትህ ተጠንቀቅ፥ በእነዚህም ጽና፤ ይህን ብታደርግ፥ ራስህንም የሚሰሙህንም ታድናለህና።